የቀብር ስፍራዎች መናፈሻ ሊሆኑ ነው ተባለ፡፡
በአዲስ አበባ ዘላቂ ማረፊያ የሆኑ የቀብር ስፍራዎች የሚያምር ገፅታ ኖሯቸው መናፈሻ እንዲሆኑ እየተሰራ ቢሆንም ‘’ሙታንን የሚያውኩ ነገሮች’’ በህግ ያስቀጣሉ ተብሏል፡፡
የቀጨኔ ዘላቂ ማረፊያ ውስጥ ገብተው በመጨፈር ማህበራዊ ትስስት ሚድያ ላይ የለቀቁ ግለሰቦችም በህግ ጥላ ስር መሆናቸውም ለዚህ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
ቀብር የሚፈፀምባቸው ስፍራዎች በአብዛኛው ሰወር ያሉ፣ በደንና ቁጥቋጦዎች የተሞሉ እንደመሆናቸው አስገድዶ መድፈርና ሌላውም ወንጀል ሲፈፀምባቸው እንደነበር ሲነገር ይደመጣል፡፡
እነዚህን ስፍራዎች ከነበራቸው አስፈሪ ገፅታ ወደ መናፈሻነት ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን በአዲስ አበባ ካሉ የቀብር ስፍራዎች መካከል አንዱ የሆነው የቀጨኔ ዘላቂ ማረፊያ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ድሪባ ገመቹ ነግረውናል፡፡
‘’እውነት ነው የቀብር ስፍራዎቹ ለወንጀል ድርጊት የተመቹ ነበሩ፤ አሁን ግን ቦታውን ወደ መናፈሻነት ቀይረነዋል፣ ባሉን 17 የሚደርሱ የጥበቃ ባለሙያዎች ጥብቅ ቁጥጥር እያደረግን ነው’’ ብለዋል፡፡
ቦታው ሰዎች ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ አስከሬናቸው በክብር እንዲያርፍ ታስቦ የተሰናዳ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ድሪባ ‘’ምንም አይነት ሙታንን የሚረብሹ ተግባራት’’ በህግ የሚያስጠይቁ መሆኑን በቅርቡ በመቃብር ስፍራው ሲጨፍሩ በመቅረፅ በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ ሰዎችን ጉዳይ በማንሳት አስረድተዋል፡፡
ህገ-ወጥ ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ከሆነ በቅርቡ በቀጨኔ ዘላቂ ማረፊያ የተፈፀመው በመቃብር ስፍራ በመጨፈር ሙታንን የማወክ ተግባር እንዴት ተፈጠረ? ላልናቸው አቶ ድሪባ ይህንን መልሰዋል፡፡
የቀጨኔ ዘላቂ ማረፊያ በአዲስ አበባ ላሉ 10 ክፍለ ከተማዎች የቀብር አገልግሎት እየሰጠ እንዳለ ከአስተባባሪው ሰምተናል፡፡
የቀጨኔን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ስር የሚተዳደሩ 15 ያህል ዘላቂ ማረፊያዎች አሉ፡፡
በዘላቂ ማረፊያዎቹ መደበኛ የቀብር አገልግሎት፣ የባይተዋር (ቀባሪ የሌላቸው በህመምም ሆነ በድንገተኛ አደጋ ህይወታቸው አልፎ ቤተሰቦቻቸው ያልተገኙ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቀብር ማስፈፀም፣ የግብዓተ መሬት ማስረጃ መስጠት፣ የሙታን መረጃ መስጠት፣ 7 ዓመት ሞልቷቸው የሚነሱ አፅሞችን ወደ ዴፖ የማዛወር ስራን በዋነኛነት የሚሰራ ነው ተብሏል፡፡
ዘላቂ ማረፊያዎቹንም በዘመናዊ መልክ በመስራት ቀብር ለመፈፀም ለሚመጡ ሰዎች ማረፊያ የሚሆኑ ቦታዎችን በማዘጋጀት በአጠቃላይ ደረጃቸውን የጠበቁ የዘላቂ ማረፊያ ስፍራዎችን አስገንብቶ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ማድረጉን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments