top of page

ህዳር 19፣2016 - የ5ጂ የሞባይል አገልግሎት በጅግጅጋ ከተማ በይፋ ስራ ጀምሯል

የአምስተኛው ትውልድ የሞባይል አገልግሎት በሱማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ በይፋ ስራ ጀምሯል፡፡


ኢትዮ ቴሌኮም ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ እና አዳማ በይፋ ለአገልግሎት ያበቃውን የዘመኑ የመጨረሻው የ5ኛ ትውልድ የሞባይል የኢንተርኔት አገልግሎት በምስራቅ ምስራቅ ሪጂን በጅግጅጋ ከተማ ተዘርግቷል ተብሏል።


በሶማሌ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር ቢሮ፣ ሆደሌይ (ቤተ-መንግስትና አየር መንገድ)፣ በሸህ አብዱሰላም ት/ቤት፣ በክልሉ ም/ቤት (ፓርላማ) አዳራሽ፣ በክልሉ ገቢዎች ቢሮ፣ በአሮጌው ታይዋን እና በኢትዮ ቴሌኮም የምስራቅ ምስራቅ ሪጂን ጽ/ቤት አካባቢዎች አገልግሎቱ እንደተጀመረ ሰምተናል።


በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ፣ በጅግጅጋ ሽህ ሐሰን ያባሬ ሪፈራል ሆስፒታል፣ በአዲሱ ታይዋን፣ ቀበሌ 06 (አህመድ ጉሬይ ት/ቤት) እና ጀላባ አካባቢዎች ደግሞ በቅርቡ አገልግሎቱን ያስጀምራል ተብሏል፡፡


የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት እስከ 10 ጊ.ባ በሰከንድ(Gbs) የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት አለው።


ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን እጅግ በላቀ ሁኔታ እንደሚቀንስ ተነግሮለታል፡፡


በአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር ውስጥ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ በርካታ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እርስ በርሳቸው ለማገናኘት የሚያስችል ዘመናዊ የገመድ አልባ ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ነው፡፡


5ጂ አገልግሎት በተለይም ወሳኝ ተልዕኮ ላላቸው (Mission Critical) እና በተመሳሳይ ወቅት (real time) መከናወን የሚፈልጉ አገልግሎቶችን ለአብነትም የማምረቻ ፋብሪካዎች፣ ግብርና፣ ህክምና፣ ለመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎች እጅግ የላቀ ፋይዳ አለው ተብሏል።


የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የ 5ጂ አገልግሎት ስራ ላይ መዋል የቢዝነስ ደንበኞችን ምርታማነታቸውን እና የአሠራር ቅልጥፍናቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ያሳድግላቸዋል ብለዋል።

በዘመናዊ መተግበሪያዎች አማካኝነት አዳዲስ ገቢዎችን እንዲያገኙ ለማስቻል፣ የቢዝነስ ትንታኔን በቀላሉ በማግኘት ከንግድ ለውጦች ጋር በፍጥነት እንዲላመዱ ያግዛቸዋልም ብለዋል።

ሕይወት ያቀላል የተባለው 5ጂ ለዘመናዊ ቤት፣ ለስማርት የጤና አገልግሎት እና የሆስፒታል አስተዳደር፤ ለስማርት ግብርና፣ ትምህርት፣ ኢንደስትሪ/ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ለስማርት ኤርፖርትና የጉዞ አገልግሎት፣ ለስማርት ትራንስፖርት፣ ለብሮድካስቲንግና ለመዝናኛ እንዲሁም በክላውድ ላይ ለተመሰረቱ የ5ጂ ጌሞች ከፍተኛ ፋይዳ ያለው የመጨረሻው ቴክኖሎጂ ነው፡፡



ተህቦ ንጉሴ



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz


Comments


bottom of page