‘’መምህራን ሳይማረሩ፣ ሳይቸገሩ፣ እና ሳይራቡ ክፍል ገብተው የሚያስተምሩበት ሀገር ማየት ምኞቴ ነው’’ መምህር እና በፓርላማው የሰው ሀብት እና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል
ፓርላማው እስካሁን በመምህራን ጥያቄ ዙሪያ ‘’እንዲህ ይሁን ያለው ነገር የለም’’ ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እስከ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ መምህራን የሚከፈላቸው ደመወዝ ስራቸውን የሚመጥን ካለመሆኑ አለፎ የዕለት ተዕለት ኖሯቸውን ለመግፋት የሚያስችላቸው እንዳልሆነ ሲናገሩ ዓመታት ቆጥረዋል፡፡
ከቀርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ቀድሞ የነበረው የደመወዝ ያንሰናል ጥያቄ ሊስተካከል ቀርቶ እንዲያውም በእንዳንድ በመንግስት ትምህርት ቤት የሚስተምሩ መምህራን ለወራት የሰራንበት ደመወዛችን እየተከፈለን አይደለም ሲሉ እየተደመጡ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፤ መምህራኑ የተለያዩ ችግሮች እየገጠሟቸው መሆኑን ጠቅሶ በአንዳንድ አካባቢዎች መብታቸው የጠየቁት ላይም እንግልትና ማዋከብ እንደሚደርስባቸው ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ ባካሔደው ስብሰባ ላይ ተናግሯል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴርም መምህራን የሚገጥሟቸው ችግሮች እንዳሉ ተረድቻለሁ ቢልም እስካሁን ግን በጥቅማጥቀምም ሆነ በደመወዝ ጭማሪ ላይ የተለየ ነገር አልታየም፡፡
ከት/ት ሚኒስቴር ባሻገር ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት እና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው፡፡ ፓርላማው የመምህራኖቹን ጥያቄ እንዴት ይመለከተዋል ስንል ጠይቀናል፡፡
ታደሰ በዛ(ዶ/ር) በፓርላማው የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ በሞያቸው ደግሞ መምህር ናቸው፡፡
‘’በሌሎች ሀገራት ለመምህራን ልዩ ክብርና ጥቅማ ጥቅም ይሰጣቸዋል፤ በኢትዮጵያም ይህ ሊደረግ ይገባል’’ ያሉን ዶ/ር ታደሰ ‘’ነገር ግን እስካሁን ቋሚ ኮሚቴው በመምህራን ጥያቄ ዙሪያ ‘’እንዲህ ይሁን ያለው ነገር የለም’’ ብለውናል፡፡
‘’መምህራን ሳይማረሩ፣ ሳይቸገሩ፣ እና ሳይራቡ ክፍል ገብተው የሚያስተምሩበት ሀገር ማየት ምኞቴ ነው’’ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
‘’ለዚህም ደግሞ የመምህራን ማህበር ድምፅ ይሆናቸዋል ብዬ አስባለገሁኝ’’ በማለት አስረድተዋል፡፡
‘’ከማህበሩ ጋር በተለያየ አጋጣሚ እንገናኛለን፤ በቅርቡም ውይይት ሊኖረን ይችላል፣ በዚያ ውይይት የመምህራኑን ችግሮች እና ተያያዥ ጉዳዮች እናነሳለን’’ ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
የመምህራን ደመወዝ በጊዜ አለመከፈልና ያለፈቃዳቸው ከደመወዛቸው መቆራረጥ፣ በትርፍ ሰዓት ክፍያ ላይ ተደራራቢ ግብር መቁረጥ፣ የመምህራን የቤትና የመስሪያ ቦታ ጥያቄ ምላሽ መዘግት እንዲሁም የመጽሀፍና የሌሎች የትምህርት ግብዓቶች እጥረት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር እየገጠሙኝ ነው ብሎ ከሚጠቅሳቸው ችግሮች መካከል ናቸው፡፡
በተጨማሪም የሞያ ማህበሩ በረቂቅ ደረጃ ባለው የትምህርት ፖሊሲ ላይ ሀሳብ እንድሰጥ በመንግስት አልተጠየቅኩም ብሏል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments