በኢትዮጵያ ከ80 በላይ ቋንቋዎች ይነገራሉ ተብሎ ይታመናል፤ እነዚህ ቋንቋዎችም ከመግባብያነት ባለፈ በማህበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ሁነቶቻችን ውስጥ ያለቸው ድርሻም ከፍ ያለ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የቋንቋው ዘርፍ የሚመራበት የመጀመርያውን ፖሊሲ ያጸደቀችው በ2012 ዓ.ም ቢሆንም እስካሁን ግን በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን ሰምተናል፡፡
ፖሊሲው ከጸደቀ ከ5 ዓመት በላይ ሆኖት እያለ በሚገባ ተግባራዊ ሊሆን ያልቻለበት ምክንያ ምንድነው ስንል በባህል እና ስፖርት ሚንስቴር የቋንቋ እና ትርጉም ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ከፍያለው አብዲሳን ጠይቀናቸዋል፡፡
እርሳቸውም ከዚህ ቀደም ከሚኒስቴር መስርያ ቤቱ እስከ ወረዳ ድረስ የተዘረጋ የቋንቋ ዘርፍ የሚመራበት አደረጃት ሳይኖር መቆየቱ በፍጥነት ወደ ስራ መግባት እንዳይቻል ያደረገ ምክንያት መሆኑን ነግረውናል፡፡
‘’ሌላው ደግሞ ዘርፉ በራሱ ሰፊ ስራ እና ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሂደትን የሚጠይቅ መሆኑ ነው ያሉ’’ ሲሆን ‘’ፖለቲከኛ ነን የሚሉ ግለሰቦች የቋንቋ ጉዳዮችን ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በያያዝ የሚፈጥሯቸው ችግሮችም የፖሊሲውን አተገባበር አዘግይቶታል’’ ብለዋል፡፡
የቋንቋ ልማት ፖሊሲው ለተግባራዊነቱ የበርካታ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተሳትፎን የሚጠይቅ እንደመሆኑ መጠን በተቋማቱም ሆን በአብዛኛው ማህበሰረብ በኩል ስለፖሊሲው እና አተገባበሩ ያለው ግንዛቤ በቂ አለመሆን ሊላኛው ምክንያት እንደሆነም አቶ ከፍያለው ነግረውናል፡፡
ለዚህም በያዝነው 2017 በጀት ዓመት የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የውይይት መድረኮች እየተካሄዱ መሆኑንም ነግረውናል፡፡
ፖሊሲው ከጸደቀ ጀምሮ እስካሁን በቂ ስራ የተሰራ ባይሆንም ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ፖሊሲው ተግባርዊ የሚሆንበትን ፍኖተ ካርታ እንዲሁም መመርያዎች ሲያዘጋጅ መቆየቱን አንስተው በቅርቡም እንዚሁ መመርያዎች ጸድቀው ወደ ስራ ይገባል ብለውናል፡፡
አዲሱ የቋንቋ ፖሊሲ 11 ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን ከእነሱም መካከል ቋንቋ እና ትምህርት፣ የትርጉም እና አስተርጓሚ ዘርፍ፣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን የቋንቋ አጠቀም ጉዳይ ፖሊሲው ትኩረት ያደረገባቸው ጉዳዮች እንደሆኑም ሰምተናል፡፡
Comentários