ትናንት እሁድ ህዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም የዓለም የኤድስ ቀን በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በተከበረበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ በቫይረሱ ስርጭትና መቆጣጠር ምን ደረጃ ላይ ናት? የሚለው ተነስቷል።
በወቅቱም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ2016 ዓ.ም በኤችአይቪ ዙሪያ ያደረገው ጥናታዊ ትንቢያ በጤና ሚኒስቴር የስራ ሀላፊዎች ይፋ ተደርጓል።
በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች ቁጥር 605,238 ደርሷል።
በየዓመቱም 7,428 ሰዎች በቫይረሱ እንደሚያዙ የኢንስቲትዩቱ ጥናት ያሳያል።
የዓለም የኤድስ ቀን በተከበረበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ደረጀ ዱጉማ(ዶ/ር) ይህንኑ ጥናት ዋቢ በማድረግ የስርጭቱ ሀገራዊ ምጣኔ በመቶኛ ከ1 በመቶ በላይ ከነበረበት ቀንሶ አሁን 0.87 በመቶ መሆኑን ጠቅሰዋል።
''ይህ ውጤት የመጣው እና ከወረርሽኝ ደረጃ መውጣት የቻልነው በሰራናቸው የኤችአይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች ነው'' ብለዋል።
ከተቀመጠው አዲስ የመያዝ ምጣኔ በ3.25 በመቶ የመያዝ ምጣኔ አዲስ አበባ ቀዳሚ ስትሆን የጋምቤላ ክልል በ3.24 በመቶ ሁለተኛ ደረጃን ላይ ነው፣ ሃረሪ፣ ድሬዳዋ፣ ትግራይና የአማራ ክልሎችም ከ3ኛ እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ የቫይረሱ ስርጭት ከፍ ብሎ የታየባቸው 6 ክልሎች መሆናቸውን ሰምቸናል።
ዝቅተኛው የ0.1 በመቶ ስርጭት የታየው በሶማሌ ክልል መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
በከተማና በገጠር የተቀመጠው የስርጭት ምጣኔ እንደሚያሳየው በከተማ 2.9 በመቶ፣ በገጠር ደግሞ 0.4 በመቶ ነው ተብሏል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ደረጀ ገለፃ በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ እየተያዙ ካሉ የማህበረሰብ ክፍሎች አፍላ ወጣት ሴቶች አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ።
ስለሆነም የስርጭቱን መጠን ከዚህም ለመቀነስ ተለዋዋጭ የሆነውን የስርጭቱን ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ የመከላከልና መቆጣጠር ስራዎች በመንግስት ይሰራሉም ብለዋል።
36ኛው የዘንድሮ የዓለም የኤድስ ቀን "ሰብዓዊ መብትን ያከበረ የኤች አይ ቪ አገልግሎት ለሁሉም" በሚል መሪ ቃል ዲፕሎማቶች፣ በቫይረሱ ላይ የሚሰሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ሌሎችም በተገኙበት ተከብሯል።
ምንታምር ፀጋው
Comments