top of page

ህዳር 24፣2017 - በኢትዮጵያ በየዓመቱ 94,000 ሄክታር ደን ይጨፈጨፋል

የኢትዮጵያ ደን ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ የሚያስችል ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ደን ልማት ተናገረ፡፡

 

ይህ እውቅና ከተሳካ ከደን ምርቷ ለውጪ ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች በገበያ ላይ ተፈላጊነታቸው እንደሚጨምር ሰምተናል፡፡

 

ኢትዮጵያ ካላት መሬት ውስጥ 23.6 ከመቶ የሚሆነው በደን የተሸፈነ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት መረጃ ያሳያል፡፡

 

በየዓመቱ በሀገሪቱ 94,000 ሄክታር ደን ይጨፈጨፋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ደን ልማት መረጃ እንደሚያሳየው ከ2000 እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ባለው 13 ዓመት 1.2 ሚሊዮን ሄክታር ደን ኢትዮጵያ ውስጥ ወድሟል፡፡

 

እንደ ማር፣ የጫካ ቡና እና ሌሎችም የተለያዩ ምርቶችን ከደኗ ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ እያቀረበች ገቢ ታገኛለች፡፡


ነገር ግን እነዚህ ምርቶቿ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና አለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ከተፈለገ በደን ጥበቃ ላይ ከሚሰራው ‘’የፎረስት ስቴዋርድሺፕ ካውንስል’’ እውቅና ማግኘት እንዳለባቸው ባለሙያዎች ነግረውናል፡፡

 

በኢትዮጵያ ደን ልማት የሬድ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ክብሩ ይስፋ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ደን ከዚህ ተቋም እውቅና እንዲያገኝ ስራ መጀመሩን ነግረውናል፡፡

 

በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ባለ 1,000 ሄክታር መሬት ላለፉት 2 ዓመታት የሙከራ ስራ ሲሰራ ነበር፡፡

 

በኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ አሻራና ሰው ሰራሽ ደን መሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ አበረ ጠና በበኩላቸው ይህ እውቅና እውን ሲሆን ሃገሪቱ ያላት የደን ሀብት በዘላቂነት ለማልማት ያስችላታል ብለዋል፡፡


በረከት አካሉ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


 

📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g

 

 

 

 

Comments


bottom of page