70 በመቶ ገደማ የሚሆኑት የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎቻቸውን መረጃ ለትምህርት ሚኒስቴር አልላኩም ተባለ፡፡
በኢትዮጵያ በግል የከፍተኛ ትምህርት ለመስጠት ከተመዘገቡ ከ300 በላይ ተቋማት መካከል ለትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎቻቸውን መረጃ ያሳወቁት 131ዱ ወይም 30 በመቶ ገደማዎቹ ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡
በሀገሪቱ በግልም ሆነ በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥርና ተያያዥ መረጃዎች የሚመዘገቡበት የመረጃ ቋት (HEMIS) በትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጀቷል፡፡
ተቋማቱ እስካሳለፍነው ነሀሴ 30፣2016 ዓ.ም ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ሰጪ ተቋማት መረጃዎቻቸውን ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ልከው በተዘጋጀው የመረጃ ቋት እንዲያስመዘግቡ ቢነገራቸውም የሚበዙት የግል ተቋማት ግን እንዳላስመዘገቡ ሰምተናል፡፡
በአንጻሩ ሁሉም የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተማሪዎቻቸውን መረጃ ልከው ጨርሰዋል ተብሏል፡፡
በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ያላስመዘገቡ የግሎቹ ተቋማት የአንድ ወር ተጫማሪ ጊዜ(እስከ መስከረም 30 2017 ዓ.ም) ተሰጥቷቸው መረጃ እንዲልኩ በውስጥ ደብዳቤ ተልኮላቸው የነበረ ቢሆንም፤ ያሰመዘገቡት ተቋማት ብዛት ግን 131 ብቻ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ይህንን ለሸገር የነገሩት በትምህርት ሚኒስቴር የግል የከፍተኛ ትምህር ተቋማት አገልግሎት ዳይሬክተር እዮብ አየነው(ዶ/ር) ናቸው፡፡
ፖሊሲዎችን ለመቅረፅም ሆነ ለተያያዥ ጉዳዮች በሀገሪቱ ያሉ ተማሪዎች ብዛት ማወቅ ስለሚያስፈልግ መረጃዎችን በአንድ ማዕከል መመዝገብ እንደሚያስፈለግም ዶ/ር እዮብ አንስተዋል፡፡
አሁን በሂደት ላይ ያሉ፣ ወይም ቀኑ ካለፈ በኋላ መረጃዎቻቸውን የላኩ ሊኖሩ ይችላሉ እኛ ግን ዓመታዊ መጽሄት ስናዘጋጅ ያወቅናቸውም ሆኑ ያካተትናቸው እነዚህ 131ዱን ብቻ ነው ብለዋል፡፡
የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በበኩሉ ሁሉም የግል የከፍተኛ ተ/ት ተቋማት እንደ አዲስ ዳግም ምዝገባ እንዲያደርጉ ነግሯቸዋል፡፡
እስከ ቀጣዩ የታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ዳግም ካላስመዘገቡ ፍቃዳቸውን እንደሚዘርዘም ተናግሯል፡፡
እስካሁን መረጃዎቻቸው በላኩት በ131ዱ የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ብዛት 353,413 ናቸው ተብሏል፡፡
በ47ቱ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በዓሁን ሰአት የሚማሩ ጠቅላላ ተማሪዎች ቁጥር ደግሞ 450,000 ገደማ ነው ሲባል ሰምተናል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ከዚህ በፊት የተማሪዎች መረጃን በተመለከተ በተለይ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የውሸት ሪፖርት ያቀርቡልኛል ብሎ ነበረ፡፡
ለአብነትም በ2015 ዓ.ም ብቻ ተጠሪነታቸው ለመንግስት የሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች የማያስተምሯቸውን 251,000 የተማሪዎች ቁጥር ጨምረው ልከውልኛል ማለቱ አይዘነጋም፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comments