ህዳር 30፣ 2015
ቁርጥራጭ ብረቶችን፣ የሚወገዱ ተሽከርካሪዎችንና ማሽኖችን ገዝተው የሚወስዱ አቅላጭ ፋብሪካዎች ለነዳጅና ለማጓጓዣ የሚያወጡት ወጪ ተቀናሽ ሆኖ ይመለስላቸዋል ተባለ፡፡
ሐገር ቤት ያሉት የብረታ ብረት አምራቾች ያለ አገልግሎት የተከማቹ ቁርጥራጭ ማሽነሪዎችን ሲገዙ ለነዳጅና ለማጓጓዣ የሚያወጡት ወጪ እንዲመለስላቸው የአሰራር ማሻሻያ መደረጉን የማዕድን ሚኒስቴር ነግሮናል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች የጥሬ እቃ ፍለጋ ከውጭ ሀገር ማስገባት ሳይኖርባቸው ሐገር ቤት ያለውን የወደቀ ሀብት እንዲጠቀሙ መንግስት ወስኗል ተብሏል፡፡
እነዚሁ የብረታ ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ከሁሉም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ያለአገልግሎት የተከማቹ ስቲል ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችን በኪሎ በ64 ብር፤ ካስት አይረኖችን ደግሞ በኪሎ 51 ብር ከ75 ሳንቲም ከፍለው ማንሳት እንደሚችሉ ተሰምቷል፡፡
መወገድ ያለባቸውን ተሽከርካሪዎች፣ ማሽነሪዎች እና ያገለገሉ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን ደግሞ ለኪሎ 51 ብር ከ25 ሳንቲም ይጠየቃሉ ተብሏል፡፡
አልሙኒየም ብረታ ብረቶችን ደግሞ በኪሎ 120 ብር ከፍለው እንዲወስዱ የማዕድን ሚኒስቴር ለሚመድባቸው የብረታ ብረት አቅላጭ ኢንዱስትሪዎች እንዲያስተላልፉ ወስኗል፡፡
እነዚሁ ቁርጥራጭ ብረቶችና ማሽነሪዎችን የሚወስዱ የብረታ ብረት አቅላጭ ኢንዱስትሪዎች ወደ ፋብሪካቸው ሲወስዱ የሚያወጡት የትራንስፖርት ነዳጅ ወጪ ተቀናሽ ይደረግላቸዋል ተብሏል፡፡
ንብረቱን ለማስመዘን የሚያወጧቸውንም የማስመዘኛ ወጪዎች ተቀናሽ ተደርጎ እንዲሸጥላቸው መወሰኑ ተሰምቷል፡፡
የብረት አቅላጭ ፋብሪካዎቹ እነዚህን ወጪዎች
በሰነድ አስደግፈው ሲያቀርቡ ጠቅላላ ከሚከፍሉት ክፍያ ላይ ተቀናሽ ተደርጎ እንዲሸጥላቸው እና ቀሪው ገንዘብ ወደ ማዕከላዊ ግምጃ ቤት እንዲገባ መወሰኑንም የማዕድን ሚኒስቴር ለሸገር ነግሯል፡፡
ተህቦ ንጉሴ
ሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Comentarios