top of page

ህዳር 4፣2016 - ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የንግድ ምልክቱን በአዲስ ቀየረ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ባለፉት 15 ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን የንግድ ምልክት በአዲስ ቀየረ።


የንግድ ምልክቱን መለወጥ ያስፈለገው ዘመኑንና የኩባንያውን ሁለንተናዊ የእድገት ደረጃ በሚመጥን መልኩ ለማድረግ ነው ተብሏል።


ዓላማውም ኩባንያው የበለጠ የደንበኞች ዓዕምሮ ውስጥ በተለየ ሁኔታ አንዲሳልና ለየት ባለ ሁኔታ እንዲታወቅ ለማድረግ ታስቦ መሆኑ ተነግሯል።


አዲሱ የኦሮሚያ ኢንሹራንስ የንግድ ምልክት የተዋቀረው ጥንታዊ እና ባህላዊ ነገር ግን ለዘመናዊው የአኗኗር ዘይቤ መሠረት የሆነውን በኢትዮጵያ በተለያየ አካባቢ በተለያዩ ስሞች የሚጣራውን ከቦራቲ የአንገት መደገፊያ ነው፡፡


ይህ በአፋን ኦሮሞ ቦራቲ የሚባለው፣ በተለይ አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አካባቢ ሲተኙ ለአንገታቸው ድጋፍ የሚጠቀሙበት ሲሆን በይበልጥ ደግሞ ሴቶች ጸጉራቸው እንዳይባላሽባቸው ማታ አንገታቸውን ተደግፈው የሚተኙበት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

እቃው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን በእጃቸው ይዘው ስለሚዞሩ ቀን ቀን እንደ መቀመጫና ማረፊያም ይገለገሉበታል፡፡


መደገፊያው በኢትዮጵያም በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ በተለያዩ ማህበረሰብ ዘንድ በተለያዩ መጠሪያዎች ይታወቃል።


ይህ ለማረፊያ፣ ለመደገፊያ የሚውል እቃ የኦሮሚያ ኢንሹራንስን እሴትና ፋይዳን ይወክላል የተባለ ሲሆን ኩባንያው የሚሰጠው እረፍት፣ ዋስትናና የአዕምሮ ሠላምን በመሆኑ አዲሱ የንግድ ምልክት ለድንበኞችም እረፍትን የሚሰጥ መሆኑ ተጠቅሷል።


አዲሱ የኦሮሚያ ኢንሹራንስ የንግድ ምልክት ‘’ስቱዲዮኒት’’ በተባለ ሀገር በቀል አማካሪ ድርጅት አማካኝነት መሰራቱ የተነገረ ሲሆን በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን መመዝገቡም ተነግሯል።

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በ2015 የበጀት ዓመት 1.7 ቢሊዮን ብር የአረቦን ገቢ መሰብሰቡን ተናግሯል።


የኩባንያው ጠቅላላ ሀብት 3.8 ቢሊዮን ብር፤ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 870 ሚሊዮን ብር መድረሱ በንግድ ምልከት ማስተዋወቂያ ፕሮግራም ላይ ሲነገር ተሰምቷል።


ኩባንያው ሜክሲኮ አካባቢ ባለ 40 ወለል የዋና መሥሪያ ህንፃ እየገነባ መሆኑን የተናገረ ሲሆን የግንባታው አጠቃላይ ወጪ አሁን ባለው ገበያ ከ6 ቢሊየን ብር በላይ ይፈጃል፣ ግንባታው እስካሁን ከ1 ቢሊዮን በላይ ወጪ ተደርጎበታል ተብሏል፡፡


ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ሁሉን አቀፍ የመድህን አገልግሎት (የጠቅላላ መድን ፣የሕይወትና የጤና መድን ፤ ማይክሮ ኢንሹራንስና በሸሪዓ ሕግጋት የሚመራውን የታካፉል ኢንሹራንስ) በመስጠት በሀገሪቱ ብቸኛዉ የመድን ኩባንያ ነኝ ብሏል።


ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግብርና ዘርፉ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በቋሚነት የሰብልና የቤት እንስሳት ኢንሹራንስ በመስጠት እንደሚታወቅ አስረድቷል።




የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz



Comments


bottom of page