top of page

ህዳር 4፣2017-በአዘርባጃን እየተካሄደ በሚገኘው በኮፕ 29 ጉባኤ ላይ የተገኙ ፕሬዘዳንት ታዬ አፅቀስላሴ “ከጉባኤው የምንጠብቀው ቃል መግባትን ሳይሆን ተጨባጭ የሆነ የፋይናንስ አቅርቦትን ነው” ማለታቸው ተሰማ

በአዘርባጃን እየተካሄደ በሚገኘው በኮፕ 29 ጉባኤ ላይ የተገኙ ፕሬዘዳንት ታዬ አፅቀስላሴ “ከጉባኤው የምንጠብቀው ቃል መግባትን ሳይሆን ተጨባጭ የሆነ የፋይናንስ አቅርቦትን ነው” ማለታቸው ተሰማ፡፡


የኢፌድሪ ፕሬዘዳንት ታዬ አፅቀስላሴ በአዘርባጃን ባኩ እየተካሄደ ከሚገኘው የኮፕ 29 ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር በተለይም ታዳጊ ሀገራት የሚያስፈልጋቸው ቃል ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ የሆነ የፋይናንስ ድጋፍ ነው ማለታቸው ተነግሯል፡፡


የአፍሪካ ሀገራትና ሌሎች በተመሳሳይ ታዳጊ የሆኑ ሀገራት በየጊዜው በሚደረጉ የአየር ጠባይ ለውጥ ጉባኤዎች ላይ የሚገባው ቃል ወደ ተግባር እንዲቀየር እና ተጨባጭ የፋይናንስ ድጋፍን ይፈልጋሉ ያሉት ፕሬዘዳንት ታዬ ይህ ካልሆነ ግን ችግሩን ለብቻቸው መጋፈጥ ይከብዳቸዋል ሲሉ መናገራቸውን የአዘርባጃን የወሬ ምንጮች ተናግዋል፡፡


ባለፉት ሶስት አመታት ኢትዮጵያ በረሃማነትን ለመከላከል በሰራቸው ስራ የደን ሀብቷን ከ17.2 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ ማሳደጓንና በ2030 እድገቱን ወደ 30 በመቶ ከፍ ለማድረግ እየሰራች ነው ሲሉ ፕሬዘዳንት ታዬ ተናግረዋል፡፡


በየጊዜው በሚደረጉ ጉባኤዎች ላይ ሀገራት ተስፋ ከመስጠት እና ቃል ከመግባት ወደ ኋላ ባይሉም ተጨባጭ የሆነውን የፋይናንስ ድጋፍ መስጠት ላይ ግን ችግሮች አሉ ሲሉም ፕሬዘዳንት ታዬ ተናግረዋል፡፡


በአዘርባጃን ኮፕ 29 ጉባኤ ላይ የቻይናና የአሜሪካ እንዲሁም ከፍተኛ ካርቦን አመንጭ የሆኑ ሀገራት መሪዎች አለመገኘታቸው ታውቋል፡፡


በፓሪሱ የአየር ጠባይ ለውጥ ጉባኤ መሰረት ከፍተኛ የካርቦን ጋዝ አመንጭ የሆኑ ሀገራት የጋዝ የልቀት የሙቀት መጠናቸውን ከ2 ከዲግሪ ሴልሺየስ በታች እንዲያደርጉ እንዲሁም ከፍተኛ ካርቦን አመንጭ የሆኑ ሀገራት የፋይናንስ የቴክኒክና ሌሎች ድጋፎችን ለታዳጊ ሀገራት እንዲሰጡ እ.ኤ.አ 2015 በኮፕ 21 ፓሪስ ላይ ስምምነት መደረሱ ይታወሳል፡፡


የኔነህ ሲሳይ

Comments


bottom of page