top of page

ህዳር 4፣2017-ባሳለፍነው ሰኞ ህዳር 2 ቀን 2017ዓ.ም በመርካቶ ገበያ ያሉ ነጋዴዎች ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ነው የመጣነው ያሉ ሰዎች ያለ ደረሰኝ ለምን ሸጣችሁ በሚል እቃችንን ወርሰውብናል ማለታቸው ይታወሳል

ባሳለፍነው ሰኞ ህዳር 2 ቀን 2017ዓ.ም በመርካቶ ገበያ ያሉ ነጋዴዎች ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ነው የመጣነው ያሉ ሰዎች ያለ ደረሰኝ ለምን ሸጣችሁ በሚል እቃችንን ወርሰውብናል ማለታቸው ይታወሳል፡፡


በዚህና ተያያዥ ምክንያቶች በእለቱ በመርካቶ ያሉ በርከት ያሉ ሱቆች ዝግ ሆነው ውለዋል፡፡


ጉዳዩን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በሰጠው መግለጫ የተባለው ችግር በመርካቶ እንደተፈጠረ አምኖ ነገር ግን የነጋዴዎችን እቃ ወርሰዋል የተባሉት ግለሰቦች ከገቢዎች ቢሮም ይሁን ከየትኛውም የመንግስት አካል ያልተወከሉ ህገ ወጦች ናቸው ብሏል፡፡


በቢሮው የታክስ ኢንቴሌጀንስና ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋዬ ነጋሽ እኛ ምንም አይነት ንብረት የመውረስ መብት የለንም መወረስ ካለበትም ይህንን የሚሰራው የጉምሩክ ኮሚሽን ነው ብለዋል፡፡


ግለሰቦቹ ከአንዳንዶቹ ነጋዴዎች ባዘጋጁት ተሽከርካሪ እቃዎችን ጭነው ሄደዋል፤ ከአንዳንዶቹ ነጋዴዎች ደግሞ ገንዘብ ተቀብለው ተሰውረዋል ያሉት ኃላፊው ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ነጋዴዎቹ ለፀጥታ አካላት መረጃዎችን በመስጠት ተባባሪ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡


በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች መንግስት ከመርካቶ ገበያ የነጋዴዎችን እቃ መውረስ ጀመረ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው ያሉት ኃላፊው ውዥምብሩ የተፈጠረው በዚህ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡



ኃላፊው የተፈጠረውን ሲያስረዱም የከተማዋ ገቢዎች ቢሮ ከዚህ ቀደም ይሰራ እንደነበረው ያለ ደረሰኝ ግብይት እንዳይፈፀም ለማድረግ ያለመ የቁጥጥር ስራ ነው ብለዋል፡፡


ከዚህ ቀደም ይህ ስራ ሲሰራ የነበረው በአለፍ ገደም ነበር፤ አሁን ምንም ዓይነት ግብይት ያለ ደረሰኝ እንዳይከወን ለማድረግ ከህዳር 1 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ መልክ የጀመርነውን ስራ ከመርካቶ በመጀመራችን ይህንን ነው ያደረግነው ብለዋል፤ አቶ ተስፋዬ፡፡


ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የመርካቶን የንግድ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች ያለ እጅ መንሻ የማሰሩ መሆኑን አረጋግጫለሁ ያለው ቢሮው ሁሉንም የመርካቶ ተቆጣጣሪዎችን በማንሳት በአዲስ መተካቱንም ተናግሯል፡፡


ቢሮው እየሰራሁ ባለው የቁጥጥር ስራ ያለ ደረሰኝ ሲገበያይ የተገኘን ማንኛውም ሰው 100 ሺህ ብር እንደሚቀጣ እወቁልኝ ብሏል፡፡


መርካቶን ጨምሮ በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ያሉ አምራቾች፣ አስመጪዎችና ቸርቻሪዎች የትኛውንም ግብይት በደረሰኝ እንዲፈፅሙ ይገደዳሉ ተብሏል፡፡


በመርካቶ አካባቢ ያለው በነጋዴዎች ዘንድ የተፈጠረው ውዥምር ረግቦ ነጋዴዎች ወደስራቸው እየተመለሱ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡


የከተማዋ ገቢዎች ቢሮ በያዝነው 2017 ዓ.ም 230 ቢሊዮን ብር ከገቢ ግብር ለመሰብሰብ ውጥን ይዞ በ3 ወር ውስጥ 47 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንና ከዚህ ቀደም ገቢ በቁጥጥር ማነስም ይሁን በሌላ ገቢ የማሰበሰብባቸው የነበሩ ዘርፎችን ወደ ግብር ሥርዓቱ እያስገባሁ ነው ማለቱ ይታወሳል፡፡


ምንታምር ፀጋው

Σχόλια


bottom of page