top of page

ህዳር 9፣2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች


የአውሮፓ ህብረት የሜዴትሬኒያን እና የኤጂአን ባህሮችን የተመለከተ ካርታውን ቱርክ አጥብቃ ተቃወመችው፡፡


ቱርክ ካርታው መብታችንን የሚጋፋ ነው እንዳለችው ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡


የቱርክ ሹሞች ካርታውን ህጋዊ አይደለም፤ ተቀባይነትም የለውም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ቱርክ በባህር ወሰን ጉዳይ ከግሪክ ጋር ውዝግቧ ነባር ነው፡፡


ግሪክ የአውሮፓ ህብረት አባል አገር ነች፡፡


ቱርክ ቀድሞ ነገር የአውሮፓ ህብረት በሁለቱ አገሮች የባህር ወሰን ጉዳይ በጭራሽ አያገባውም ማለቷ ተጠቅሷል፡፡



የሊባኖሱ የጦር ድርጅት(ሔዝቦላህ) ቃል አቀባይ ሞሐመድ አፊፍ በእስራኤል የአየር ጥቃት ተገደሉ ተባለ፡፡


አፊፍ እስራኤል በሊባኖሷ ርዕሰ ከተማ ቤይሩት ማዕከላዊ ክፍል በፈፀመችው ድብደባ መገደላቸውን የደህንነት ሹሞች እንደተናገሩ አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


የሔዝቦላሁ ቃል አቀባይ የተገደሉት በቤይሩት የሶሪያው ባአዝ የፖለቲካ ማህበር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት በእስኤል የአየር ጥቃት በተመታበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡


የእስራኤል ጦር ግን በድብደባው ሞሐመድ አፊፍን ገድሏቸዋል ስለመባሉ እንዲህም ነው እንዲያም ነው አላለም፡፡


እስራኤል በሊባኖስ የተለያዩ ክፍሎች የምትፈፅመውን ድብደባ ቀጥላለች፡፡


ቀደም ሲል የሄዝቦላሁን የቀድሞ መሪ ሐሰን ናስረላህን ጨምሮ የቡድኑን ታላላቅ የጦር አዛዦች መግደሏን መረጃው አስታውሷል፡፡



ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ዩክሬይን አሜሪካ ባስታጠቀቻት ታላላቅ ሚሳየሎች ወሰን አሻግራ ሩሲያን እንድትመታ ፈቀዱላት ተባለ፡፡


ባይደን ዩክሬይን አሜሪካ ባስታጠቀቻት ታላላቅ ሚሳየሎች ወሰን አሻግራ ሩሲያን እንድትመታ መፍቀዳቸውን የዋይት ሐውስ ሹሞች ማረጋገጣቸውን CBS ፅፏል፡፡


ዩክሬይን ምዕራባዊያን ባስታጠቋት ረጅም ርቀት ተወንጫፊዎች ሩሲያን ለመምታት ቀደም ሲል ተቀምጦላት የነበረው የርቀት ገደብ እንዲነሳላት ስትጎተጉት ቆይታለች፡፡


ሩሲያም ቀደም ሲል እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ በቀጥታ ከምዕራባዊያኑ ጋር ወደ ግጭት ሊያስገባን ይችላል ስትል በተደጋጋሚ አስጠንቅቃለች፡፡


ፈረንሳይ እና ብሪታንያም ዩክሬይን የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳየሎቻቸውን ተጠቅማ በሩሲያ ላይ ወሰን ተሻጋሪ ጥቃት እንድትፈፅም ሊፈቅዱ እንደሚችሉ መገመቱ ተጠቅሷል፡፡


ባይደን ለዩክሬይን ሰጡት የተባለው ፈቃድ እስካሁን በይፋ አልተነገረም ተብሏል፡፡


የኔነህ ከበደ

Comentários


bottom of page