top of page

ሐምሌ 10፣ 2016 - ‘’ባለፉት 47 ዓመታት ሳስተዳድራቸው የነበሩ ቦታዎችን በድንገት ልቀቅ ተባልኩኝ’’ እንረዳዳ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር

‘’ባለፉት 47 ዓመታት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 አትላስ እና ደሳለኝ ሆቴል አካካቢዎች ሳስተዳድራቸው የነበሩ ሁለት ቦታዎችን በድንገት ልቀቅ ተባልኩኝ’’ ሲል እንረዳዳ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ተናገረ፡፡


ማህበሩ ቦታዎቹን ከመንግስት የተረከበው በ1969 ዓ.ም መሆኑን ተናግሮ፤ የሁለቱ ቦታዎች ስፋትም በድምሩ 8,100 ካሬ ሜትር መሆኑን አስረድቷል።


እንረዳዳ ሲመሰረት "የመኖሪያ ቤቶች ሕብረት ስራ ማህበር" ሆኖ እንደነበር የሚያስታውሱት የማህበሩ አባላት በዚህም ማህበሩ ለ147 ሰዎች ቤት መስራቱን ይጠቅሳሉ፡፡


ከቤት ግንባታው የተረፈው 8,100 ካሬ ሜትር ቦታውን እንረዳዳ የሕብረት ስራ ማህበርን በማቋቋም የተለያየ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱ ተነግሯል።


በቦታው ላይም ህንፃ በመገንባት ካፌዎች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ የህክምና መስጫ የመሳሰሉ እንደሚሰሩ የተናገሩት የማህበሩ አባላት በተቀረው ቦታ ላይ ተጨማሪ ግንባታዎች ለማካሄድ እና የማህበሩን አባላት ቁጥርም ለማስፋፋት ተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም በሸማች ማህበር ከዚህ የበለጠ መስራት አይቻልም ተብለን ቆይተናል ሲሉ ማህበሩ ሲመሰረት ጀምሮ አባል የሆኑ አቶ ታመሩ ወንድምአገኘሁ ተናግረዋል፡፡

‘’ሳቮር ሬስቶራንት’’ እና ‘’ናታኒ ካፌ’’ ያሉበትን ህንፃ ጨምሮ የሚያስተዳድረው ማህበሩ በዚህም ለ250 ሰዎች ቋሚ የስራ እድል መፈጠሩን የተናግሮ በድንገት ቦታውን እንድንለቅ፣ ተከራዮቹንም እንድናስወጣ ትዕዛዝ ተሰጥቶናል ሲሉ የማህበሩ የቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ ማንያህልሻል ከበደ ያስረዳሉ፡፡


"የአዲስ አበባ ካቢኔ ነው የወሰነው ብንባልም ደሳለኝ ሆቴል ጀርባ ላለው 2,400 ካሬ ሜትር እንጂ ሴቬር ሬስቶራንት ያለበት ጋር ያለው 5,700 ካሬ ሜትር የውሳኔ ደብዳቤ አልደረሰንም" ብለዋል፡፡


ውሳኔው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥቅምት 24/2016 መወሰኑ እና እነሱ በቃል የተነገራቸው ግን ሚያዚያ 8 /2016 ዓ.ም እንደሆነ የሚናገሩት የማህበሩ የቦርድ አባላት ይህም የሀገሪቱን ህግ የጣሰ አካሄድ ነው ይላሉ፡፡


አንድ ቦታ ለህዝብ ጥቅም ሲባል በመንግስት ሊወሰድ እንደሚችል በ2014 በወጣው መመሪያ የተጠቀሰ መሆኑን እናውቃለን የሚሉት የማህበሩ አባላት እኛ ላይ የተደረገው ግን ከመመሪያው ውጪ ነው ብለዋል።


አንድ ቦታ መንግስት ለልማት ከፈለገው ልማቱ ከመጀመሩ አንድ ዓመት በፊት፣ አስቸኳይ ከሆነ ደግሞ ከ 6 ወር በፊት የልማቱ ተነሺዎች አንዲያውቁት ይደረጋል የሚለውን መመሪያ በማስታወስ፡፡

ቦታዎቹን የማልማት አቅሙ አለን፣ ቅድሚያ እድሉን ስጡን እያልን የመንግስትን ደጅ ብንጠናም እስካሁን የሚሰማን አላገኘንም የሚሉት የእንረዳዳ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር አባላት የመንግስት ሰዎች እየመጡ አንዴ ቦታው ሲለኩ አንድ ጊዜ ልቀቁ እና ውጡ እያሉን ይገኛሉ ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።


ሸገር በጉዳዩ ላይ የቦሌ ክፍለ ከተማን ያነጋገረ ሲሆን ጉዳዩ ካቢኔ የወሰነበት በመሆኑ የእኛ ስራ ማስፈፀም ነው፤ ማብራሪያ ሊሰጥበት የሚችለውም የመሬት አስተዳደር ነው የሚል መልስ አግኝቷል፡፡

የካቢኔ ውሳኔውን ግን ለማህበሩ ሰጥተናል ሲል ክፍለ ከተማው አክሏል፡፡


ሸገር የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም፡፡



ንጋቱ ሙሉ


댓글


bottom of page