top of page

ሐምሌ 11፣ 2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች

አሜሪካ


ሁለት ሶስተኛ ያህሉ የዴሞክራቲክ የፖለቲካ ማህበር አባሎች ፕሬዘዳንት ጆን ባይደንን የመጪው ምርጫ እጩነታቸው እንዲተውት ይሻሉ ተባለ፡፡


ብዙሃኑ የዴሞክራቲ ፓርቲው አባላት ባይደን እጩነታቸውን እንዲተውት ፍላጎት እንዳላቸው በቅርቡ የተደረገን የዳሰሳ ጥናት ግኝት ዋቢ አድርጎ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡


ጆ ባይደን ቀደም ሲል ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት የቴሌቪዥን የምርጫ ክርክር ቅጥ አምባሩ ጠፍቷቸው ነበር መባሉ ለከፍተኛ ትችት አጋልጧቸዋል፡፡

የዴሞክራቲክ የፖለቲካ ማህበሩ ቱባ ቱባዎችም አንዱ ከሌላው እየተከታተሉ ፕሬዘዳንቱን በቃ እጩነቱን ተውት እያሏቸው ነው፡፡


ባይደን ግን እጩነቴን በጭራሽ አልተወውም በሚለው አቋማቸው እንደፀኑ ነው፡፡


ባይደን በአቋማቸው ከገፉበት በመጪው መስከረም ወርም ከትራምፕ ጋር የቴሌቪዥን የምርጫ ክርክር ያደርጋሉ ተብሏል፡፡


ባንግላዴሽ


የባንግላዴሽ መንግስት በሀገሪቱ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ዝግ ሆነው እንዲቆዩ አዘዘ፡፡


በአገሪቱ የመንግስት ሥራ ድልድል በተመለከተ የተነሳው ተቃውሞ መብረጃ እንዳላገኘ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡


የሰሞኑ ተቃውሞ ባስከተለው ግጭት የ6 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ታውቋል፡፡


የርዕሰ ከተማዋ ዳካ ዩኒቨርስቲ የተቃውሞው ማዕከል ነው ተብሏል፡፡


የአገሪቱ መንግስት በዚህ የተነሳ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ዝግ ሆነው እንዲሰነብቱ ማዘዙ ተሰምቷል፡፡


ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥም ዩኒቨርስቲዎቹ ዝግ ሆነው ይቆያሉ ተብሏል፡፡


ፖሊሶች የተቃውሞው አደፋፋሪ ነው ያሉትን የብሔራዊ ፓርቲ የተሰኘውን የተቃውሞ የፖለቲካ ማህበር መውረራቸው በመረጃው ተጠቅሷል፡፡


ጊኒ


የምዕራብ አፍሪካዊቱ አገር ጊኒ የህግ ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ መምታታቸው ተሰማ፡፡


የሕግ ባለሙያዎቹ ወደ አድማ ያመሩት የአገሪቱ ወታደራዊ መንግስት ጭቆናውን አክፍቶብናል በሚል ምክንያት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የጊኒ ወታደራዊ መንግስት በዜጎች ላይ ከህግ አግባብ ውጭ እስር ይፈፅማል ሲሉ የህግ ባለሙያዎቹ ተቃውሞ እያሰሙ ነው፡፡


ተይዘው ወዴት እንደደረሱ የማይታወቅ ዜጎችም አሉ ብለዋል፡፡


በዚህም ምክንያት የህግ ባለሙያዎች ወደ አጠቃላይ የስራ ማቆም አድማ ማምራታቸው ተሰምቷል፡፡


ፍርድ ቤቶችም በዚሁ የተቃውሞ አድማ ምክንያት ለ2 ሳምንታት ያህል እንደማያስችሉ ታውቋል፡፡


ጊኒ በምዕራብ አፍሪካ በወታደራዊ መንግስታት ከሚተዳደሩት አገሮች አንዷ እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡


ኬንያ


በኬንያ በባህላዊ ማዕድን ማውጫ ስፍራ በደረሰ የመደርመስ አደጋ በጥቂቱ የ5 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰማ፡፡


በርካቶች ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው ሬውተርስ ፅፏል፡፡


አደጋው የደረሰው በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል መሆኑ ታውቋል፡፡


የተደረመሰው የወርቅ ማዕድን ማውጫ ከዚህ ቀደምም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ግጭት ሲፈጠርበት የቆየ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡


በኬኒያ እንዲህ ዓይነቱ የማዕድን ስፍራ መደርመስ አደጋ ይደጋገማል ይባላል፡፡


ሒሎ በተባለ የማዕድን ማውጫ ስፍራ ባለፈው ግንቦት ወር በደረሰ ተመሳሳይ የመደርመስ አደጋ የ5 ሰዎች ህይወት ማለፉ ለትውስታ ተጠቅሷል፡፡


ሊባኖስ


የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን (ሔዝቦላህ) መሪ ሐሰን ናስረላህ እስራኤል በሊባኖስ ሲቪሎች ላይ ጥቃት ማድረሷን ከቀጠለች በእስራኤል አዳዲስ ዒላማዎችን እንመታለን ሲሉ ዛቱ፡፡


እስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻዋን ከጀመረች ወዲህ ሔዝቦላህ በቋሚነት ከእስራኤል ጋር በጦር ነገር እየተፈላለገ ነው፡፡


የሊባኖሱ የጦር ድርጅት ወደ ሰሜናዊ እስራኤል በቋሚነት ሮኬቶችን እየተኮሰ ነው፡፡


እስራኤልም በሊባኖስ ወሰን ተሻጋሪ ጥቃት እየፈፀመች ነው፡፡


ሐሰን ናስረላህ እስራኤል በሊባኖስ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃቷን ከቀጠለች እስራኤል ውስጥ አዳዲስ ዒላማዎችን እንመታለን ሲሉ ዝተዋል፡፡


እስራኤል እና ሔዝቦላህ ወደ ሙሉ ጦርነት ሊያመሩ ይችላሉ የሚለው ስጋት አለመገፈፉን ሬውተርስ ፅፏል፡፡



ቻይና


በቻይና ዚጎንጎ ከተማ በአንድ የገበያ ማዕከል ባጋጠመ የቃጠሎ አደጋ የ16 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰማ፡፡


ቃጠሎው የደረሰው በከተማዋ በሚገኝ ባለ 14 ፎቅ የገበያ ማዕከል እንደሆነ የአሜሪካ ድምፅ በድረ ገፁ ፅፏል፡፡


የአደጋ ተከላካይ ሰራተኞች 75 ሰዎችን ከሕንፃው በማውጣት ማትረፋቸው ተነግሯል፡፡


ቃጠሎው የተቀሰቀሰው ከሕንፃው የታችኛው ክፍል ነው ተብሏል፡፡


በቻይና እንደ ገበያ ማዕከል ባሉ የህዝብ አገልግሎት መስጫዎች የሚደርሰው የቃጠሎ አደጋ እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡


የዚጎንጉ የገበያ ማዕከል የቃጠሎ አደጋ በምን ምክንያት እንደተቀሰቀሰ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡


በጥር ወር በገበያ ማዕከልነት በሚያገለግል ህንፃ አጋጥሞ በነበረ ቃጠሎ የ39 ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ መረጃው አስታውሷል፡፡



የኔነህ ከበደ



Comments


bottom of page