የኬንያው ፕሬዘዳንት ዊሊያም ሩቶ ከተቃዋሚው የፖለቲካ ጥምረት ወገን የሆኑ አራት ሚኒስትሮችን በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ማካተታቸው ተሰማ፡፡
ለተቃዋሚ ፖለቲከኞቹ ተሰጥተዋል ከተባሉ የሚኒስትርነት ቦታዎች የገንዘብ እና የኢነርጂ ቁልፍ ሹመቶች እንደሚገኙበት ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ፕሬዘዳንት ሩቶ ተቃዋሚዎቹን በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ያካተቱት በአገሪቱ መንግስት ላይ ተቃውሞ ባላባራባት አጋጣሚ ነው ተብሏል፡፡
ሩቶ ቀደም ሲል የ11 ሚኒስትሮችን ዝርዝር እወቁልኝ ያሉ ሲሆን ትናንት ደግሞ አራቱን የተቃዋሚ ወገኖች ጨምሮ የ10 የካቢኔ አባላትን እወቁልኝ ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
አራቱ ተሿሚዎች ከዋነኛው የተቃውሞ ጥምረት መሪ ራይላ ኦዲንጋ ጋር ቅርበት ያላቸው እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የሁሉም ሚኒስትሮች ሹመት ተቀባይት የሚያገኘው ፓርላማው ይሁንታውን ሲሰጥ ነው ተብሏል፡፡
15 ዓመታት በኋላ ረሃብን ከምድር ገፅ ለማጥፋት የተያዘው ውጥን እንደማይሳካ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት አሳየ፡፡
ከመንፈቅ በፊት በተጠናቀቀው አመት የዓለማችን ረሃብተኞች ብዛት 733 ሚሊዮን እንደደረሰ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
ከዚህ ጊዜ ከ4 አመታት በፊት ከነበረው ሲመሳከርም የረሃብተኞቹ ብዛት በ152 ሚሊዮን ያህል ጨምሯል ተብሏል፡፡
እንደ ሪፖርቱ ከአለማችን ከእያንዳንዳቸው 11 ሰዎች አንዱ ረሃብተኛ ነው፡፡
በአፍሪካ ደግሞ ችግሩ የባሰ እንደሆነ በሪፖርቱ መጠቀሱን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
በአፍሪካ ከአምስት ሰዎች መካከል አንዱ ረሃብተኛ እንደሆነ ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡
በዚህ አዝማሚያ ከ15 አመታት በኋላ ረሃብን ከምድረ ገፅ የማጥፋቱ ውጥን ላም አለኝ በሰማይ ዓይነት ነው ተብሏል፡፡
ጦርነት ፣ የአየር ለውጥ እና የኢኮኖሚ ቀውስ በረሃብ አባባሽነት ተጠቅሰዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የአሜሪካን እንደራሴዎች ጦር ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩላቸው ጠየቁ፡፡
ኔታንያሁ ለኮንግረስ አባላቱ የጋራ ስብሰባ ንግግር ማድረጋቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ኔታንያሁ በዚሁ ንግግራቸው ጠላቶቻችን ጠላቶቻችሁ ናቸው ድላችንም ድላችሁ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኮንግረሱ ባደረጉት ንግግር ኢራንን በጠላትነት አጉልተው ማቅረባቸው ታውቋል፡፡
ኔታንያሁ ለአሜሪካ እንደራሴዎች ንግግር ያደረጉት የጋዛው ጦርነት ባስከተለው ከፍተኛ ውድመት እና እልቂት የተነሳ የሀሳብ ክፍፍሉ እየበረታ በመጣበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡
ከኮንግረሱ መምከሪያ ውጭ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ጦርነት አውጋዦች ኔታንያሁን በጦር ወንጀለኝነት በመኮነን ድምፃቸውን አጉልተው መኮነናቸው ተሰምቷል፡፡
ወደ አዳራሹ በመዝለቅ ንግግራቸውን ለማወክ ከሞከሩት መካከል 5ቱ ተይዘው መታሰራቸው ተሰምቷል፡፡
በኔታንያሁ ንግግር ወቅት በአዳራሹ ያልተገኙ ዴሞክራት እንደራሴዎች ነበሩ ተብሏል፡፡
በጋዛው ጦርነት የአሜሪካ መንግስት ለእስራኤል ታላቅ የፖለቲካ ፣ የጦር እና የዲፕሎማቲክ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ይነገራል፡፡
የኔነህ ከበደ
Comentarios