top of page

ሐምሌ 19፣2015 - ኢትዮጵያ ንግዷን የምትመራበት ፖሊሲ እያዘጋጀች ነው ተባለ



እስአ አሁን ንግድን የተመለከተ ፖሊሲ እንዳልነበረ ተነግሯል።


በውይይት ሂደት ላይ ይገኛል የተባለው ረቂቅ የንግድ ፖሊሲ ሲፀድቅ የግሉ ዘርፍ ስራ እንዲቀላጠፍ ያግዛል ተብሏል።


አገር አቀፉ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ በስካይ ላይት ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል።


የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ድኤታ አቶ ተሻለ በልሁ በመድረኩ ላይ እንዳሉት እየተዘጋጀ ያለው ፖሊሲ የግል ባለሃብቶች የሚያነሷቸውን ችግሮች ለመፍታት በእጅጉ ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


አገር አቀፉ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ የኢትዮጵያን የግብርና፣ ቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ዘርፎች ለማነቃቃት ያለመ እንደሆነ ተነግሯል።


በመድረኩ በሚካሄዱ ውይይቶች ዘርፎቹን ለማሳደግ የሚረዱ ሃሳቦች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቅሷል ።


የምክክር መድረኩን የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲሁም ከፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት ሠምተናል።


መድረኩ ባለፉት 3 ዓመታት በሀገራችን በተከሰቱ የተለያዩ ችግሮች ምክንያት ተቋርጦ እንደቆየም ተነግሯል።


ለምጣኔ ሐብታዊው ክንውን እንቅፋት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ለማስወገድ መፍትሔ ያዋጣል ተብሎ የታመነበት መድረክ በነገው እለትም እንደሚቀጥል ሰምተናል።

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፉ ማህበራት ምክር ቤት ለዚሁ ምክክር መንደርደሪያ እንዲሆነው ቀደም ብሎ ሶስት ጥናቶችን እንዳስጠና ተነግሯል፡፡


በጥናቶቹም ለወቅታዊ ምጣኔ ሐብታዊ ክንውን እንቅፋት የሆኑትን ችግሮች መለየቱ ታውቋል።



ንጋቱ ረጋሣ



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz





Comments


bottom of page