ሐምሌ 22፣2016
በነዳጅ የሚሰሩ አውቶሞቢሎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ተጥሎ የነበረው ክልከላ ተነሳ።
በኤሌክትሪክ ሞተር ከሚሰሩት በስተቀር የተገጣጠሙ የቤት አውቶሞቢሎች፣ የባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች እና የተገጣጠሙ ሞተር ሳይክሎችን ጨምሮ " ቅድሚያ የማይሰጣቸው " ተብለው የተለዩ 38 ዓይነት ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ እግድ ተጥሎ መቆየቱ ይታወሳል።
ቀደም ሲል በ38 የገቢ ንግድ ሸቀጦች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ ተነሥቷል ሲል ብሔራዊ ባንክ ተናግሯል ፡፡
ወደ ውጭ የሚደረግ የካፒታል ሂሳብ ፍሰት እንደ በፊቱ የተገደበ ቢሆንም፤ የውጭ ምንዛሪ ገበያው ለገቢ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ነጻ ሆኗል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ ማድረጉን ጠቅሷል።
በትናንትናው ዕለት መንግሥት አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን አስመልክቶ የስጠውን መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዛሬው ዕለት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻሉን አስረድቷል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ሥራ ላይ የሚውለው ይህ ማሻሻያ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ወደሆነና በገበያ ላይ ወደተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት እንደሚያሸጋግራትና በኢኮኖሚ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆየውን የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትና መዛባት እንደሚያሻሽል ታምኖበታል፡፡
የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሠረት የሚተገበር ይሆናል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ የሚከተሉትን ዐበይት አዳዲስ የፖሊሲ ለውጦችን ያካትታል፡-
1. የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ሥርዓት ይሸጋገራል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሚና፣ ገበያውን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡
2. የውጭ ምንዛሪን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማስተላለፍ ግዴታ ቀሪ ሆኗል፡፡ በመሆኑም፤ ላኪዎችና ንግድ ባንኮች ያፈሩትን የውጭ ምንዛሪ ለራሳቸው ማስቀረት ይችላሉይህም ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በእጅጉ ያሻሽላል፡፡
3. ቀደም ሲል በ38 የገቢ ንግድ ሸቀጦች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ ተነሥቷል፡፡ ወደ ውጭ የሚደረግ የካፒታል ሂሳብ ፍሰት እንደ በፊቱ የተገደበ ቢሆንም፤ የውጭ ምንዛሪ ገበያው ለገቢ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ነጻ ሆኗል፡፡
4. ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች ካፈሩት የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለራሳቸው ያስቀሩት የነበረው 40 በመቶ ወደ 50 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡
5. ቀደም ሲል ባንኮች ለተለያዩ ገቢ ሸቀጦች የሚጠቀሙበት የውጭ ምንዛሪ አሠራርና አደላደል ደንቦች ቀሪ ሆነዋል፡፡
6. አሁን በሥራ ካሉና በባንኮች ከተቋቋሙ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች (Forex Bureaus) በተጨማሪ ባንክ ያልሆኑ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ይቋቋማሉ፡፡ ለእነዚህ ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችም በገበያ ዋጋ የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ እንዲገዙና እንዲሽጡ የሥራ ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡
7. ሸቀጦችን በፍራንኮ ቫሉታ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ረገድ የተጣሉ ክልከላዎች ለማንሳት በቅርብ ጊዜ የማሻሻያ ደንብ ይወጣል፡፡
8. በውጭ ተቋማት፣ በውጭ ኢንቨስተሮች እና በትውልደ ኢትዮጵያውያን (በዳያስፖራዎች) የተከፈቱ የውጭ ምንዛሪ ሂሳቦችን አስተዳደር የሚመለከቱ በርካታ ሕጎች እንዲላሉ ተደርጓል፡፡
9. በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ከውጭ የሚላክላቸውን ሐዋላ፣ በውጭ ምንዛሪ የሚከፈል ደሞዝን/የኪራይ ገቢን እና ሌሎች ገቢዎችን የሚያስቀምጡባቸውን የውጭ ምንዛሪ ሂሳቦች እንዲከፍቱ፣ እንዲሁም እነዚህን የውጭ ምንዛሪ ሂሳቦች ተጠቅመው የውጭ አገልግሎት ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ ተፈቅዷል፡፡
10.ቀደም ሲል የግል ኩባንያዎች ወይም ባንኮች በሚወስዷቸው የውጭ ብድሮች ላይ ይከፍሉት የነበረው የወለድ ተመን ጣሪያ ተነሥቷል፡፡
11. መመዘኛውን የሚያሟሉ የውጭ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ (Ethiopian Securities Exchange) እንዲሳተፉ ተፈቅዷል፡፡
12. በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚሠሩ ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሪ ገቢያቸውን ሙሉ በሙሉ ለራሳቸው መያዝን ጨምሮ ልዩ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡
13. ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት የሚጓዙ ወይም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ሊይዙ በሚገባ የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ ተጥለው የነበሩ የተለያዩ ጥብቅ ደንቦች እንዲላሉ ተደርጓል፡፡
ንጋቱ ሙሉ
Comments