top of page

ሐምሌ 25፣2016 - መድሃኒቶችን ከሆስፒታሎች በማውጣት በግል ፋርማሲዎች ዋጋ በመጨመር የሚያቀርቡት ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ተባለ

ለመንግስት የጤና ተቋማት በነፃ ለታካሚዎች የሚቀርቡ እንደ ወባ ያሉ መድሃኒቶችን ከሆስፒታሎች በማውጣት በግል ፋርማሲዎች ዋጋ በመጨመር የሚያቀርቡት ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ተባለ፡፡


ወባ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ በቂ የመድሃኒት ስርጭት ተደርጓል መድሃኒቱም በነፃ እየተሰጠ እንደሆነ ተነግሯል፤ነገር ግን ለመንግስት የህክምና ተቋማት የሚቀርቡ መድኃኒቶችን ከዛ እያወጡ በግል የመድኃኒት መደብሮች ላይ ዋጋ በመጨመር የሚሸጡ አሉ ተብሏል፡፡


በመንግስት እንዲሁም ከለጋሽ ድርጅቶች ከሚቀርቡ መድኃኒቶች ለወባ ህክምና የሚውለው አንዱ ቢሆንም መድኃኒቱ ከጤና ተቋማት ውጪ በግል ፋርማሲዎች በብዙ ዋጋ እየተሸጠ በመሆኑ ቅሬታ አስነስቷል፡፡


በተለይ አሁን ላይ በተለያዩ ክልሎች ያለውን ከፍተኛ የወባ ስርጭት ተከትሎ በቂ የሆኑ መድኃኒቶችን ለተቋማት አቅርበናል ሲሉ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ ተናግረዋል፡፡


በህገ-ወጥ መንገድ በኮንትሮባንድ የሚገባ የወባ መድኃኒት መኖሩ ሌላው ችግር ነው ያሉት ድ/ር አብዱልቃድር ባለፉት ሁለት ወራት ከኬኒያ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የነበረ ህገ-ወጥ መድሃኒት መያዙን ተናግረዋል፡፡

የወባ መድኃኒት በመንግስት የጤና ተቋማት ላይ በነጻ የሚቀርብ ቢሆንም በህጋዊነት የሚያስመጡ የግል አቅራቢዎችም መኖራቸው የተነገረ ሲሆን በግሎቹ ላይ ለሚሸጡት ጥራታቸውንና ህጋዊነታቸውን በተመለከተ በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡


ለመንግስት ተቋማት የሚቀርቡት ላይም የተለየ መለያ የሚደረግባቸው በመሆኑ በግል መደብሮች ላይ ካጋጠማቹ ለተቆጣጣሪው አካል እንድታሳውቁ ሲል አገልግሎቱ አሳስቧል፡፡


ምህረት ስዩም



Comments


bottom of page