በቶጎ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ተሾሙ፡፡
በፕሬዘዳንት ፋውሬ ንያሲምቤ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት ቪክቶሪ ቶሜጋ ዶግቢ እንደሆኑ አናዶሉ ፅፏል፡፡
በአዲሱ የአገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት አገሪቱ ባለ ጠቅላይ ሚኒስትር ስትሆን የአሁኑ የመጀመሪያዋ ነው ተብሏል፡፡
ቶሚጋ ዶግቤ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ለቶጎ ብቻ ሳይሆን ለምዕራብ አፍሪካ ክፍለ አህጉርም የመጀመሪያ እንደሆኑ ታውቋል፡፡
የቶጎዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፉት 16 አመታት በተለያዩ የሚኒስትርነት ሀላፊነቶች ማገልገላቸው ተጠቅሷል፡፡
አዲሱ የቶጎ ህገ መንግስት የአገሪቱ ፕሬዘዳንቱ በፓርላማው እንዲመረጥ የሚጠይቅ መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡
ሩሲያ እና ምዕራባዊያን ታላቅ የተባለ የእስረኞች ልውውጥ አደረጉ፡፡
ሩሲያ 16 የምዕራባዊያን አገሮችን እስረኞች ስትለቅ በምላሹ 8 ሩሲያውያንን መረከቧን ቢቢሲ አውርቷል፡፡
ሩሲያውያኑ በብርቱ ብርቱ ወንጀሎች በአሜሪካ ፣ ኖርዌይ ፣ ጀርመን ፣ ፖላንድ እና ስሎቬኒያ ታስረው የቆዩ እንደነበሩ ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
ከተለቀቁት 16 የምዕራባዊያን አገሮች እስረኞች መካከል በቅርቡ በስለላ የ12 አመታት እስር ተፈርዶበት የነበረው አሜሪካዊው የዎል ስትሪት ጋዜጠኛ ኢቫን ለልዋጩ ጌርሽኮቪች አንዱ ነው ተብሏል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ለአሜሪካ ዜጎች ነፃ መውጣት ለልዋጩ ሩሲያውያኑን እስረኞች በመልቀቅ የረዱትን የአውሮፓ አገሮች ማመስገናቸው ተሰምቷል፡፡
የተለቀቁት የሩሲያ እስረኞች አገራቸው ሲገቡ ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአካል ኤርፖርት በመገኘት የእንኳን ነፃ ወጣችሁ አቀባበል አድርገውላቸዋል ተብሏል፡፡
በሩሲያ እና በምዕራባዊያኑ መካከል የተደረገው የእስረኞች ልውውጥ ታሪካዊ እየተሰኘ ነው፡፡
ቱርክም የእስረኞች ልውውጡን በማቻቸት እየተወደሰች ነው ተብሏል፡፡
የፍልስጤማውያኑ የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት መሪ ኢስማኤል ሐኒያ የተገደሉት በቴህራን በሚገኘው የማረፊያ ቤታቸው በድብቅ ተጠምዶ በነበረ ፈንጂ ነው ተባለ፡፡
ቀደም ሲል ሐኒያ የተገደሉት እስራኤል ከጎሕ መቅደድ አስቀድሞ በፈፀመችው የአየር ድብደባ ነው ተብሎ እንደነበር ዘ ቴሌግራፍ አስታውሷል፡፡
ሐኒያ ባረፉበት ቤት ተጠምዶ በነበረ ፈንጂ መገደላቸውን በስም ያልተጠቀሱ የአሜሪካ እና የኢራን ሹሞች እንደተናገሩ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
በሐኒያ ላይ ግድያውን የፈፀመችው እስራኤል ነች ብትባልም እሷ ግን በዚህ ጉዳይ እስካሁን ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልሰጠችም፡፡
ትናንት በቴሕራን ለእስማየል ሐኒያ አስከሬን ታላቅ የስንብት ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል፡፡
ቋሚ መኖሪያቸውን ሆና በቆየችው ካታር ዛሬ የቀብራቸው ሥነ-ሥርዓት እንደሚፈፀም ታውቋል፡፡
የሊባኖሱ የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት /ሔዝቦላህ/ መሪ ሐሰን ናስረላህ እስራኤል የሐማሱን መሪ እስማዮ ሐኒያን እና የሄዝቦላሁን ከፍተኛ የጦር አዛዥ ፉአድ ሹከርን መግደሏን ቀይዋን መስመር ያለፈችበት ድርጊት ነው አሉ፡፡
እስራኤል ፉአድ ሹከርን መግደሏን እወቁልኝ ያለችው ሳታረፍድ ነው፡፡
በኢራኗ ርዕሰ ከተማ ቴሕራን የተገደሉትን የሐማሱን መሪ ኢስማየል ሐኒያን ግድያ በተመለከተ ግን ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልሰጠችም፡፡
ፉአድ ሹከር የሄዝቦላሁ መሪ ሐሰን ናስረላህ የወታደራዊ ጉዳዮች አማካሪ እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
በሔዝቦላሁ ከፍተኛ የጦር አዛዥ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ወቅት ናስረላህ ከእስራኤል ጋር ግጭታችን አሁን ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
አፀፋውም አይቀርም ብለዋል፡፡
በቀጠናው ውጥረቱ እየተባባሰ እና የጦርነት ስጋቱም እያየለ ነው፡፡
በሐማሱ መሪ ግድያ ምክንያት የኢራን ሹሞችም የብቀላ ዛቻ እያሰሙ ነው፡፡
የኔነህ ከበደ
Comments