top of page

ሐምሌ 29፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Aug 5, 2024
  • 2 min read

የናይጀርያው ፕሬዘዳንት ቦላ ቲኑቡ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ፡፡


ተቃውሞው የተነሳው በአገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት አልቻልነውም ባሉ ዜጎች እንደሆነ አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


ፕሬዘዳንት ቲኑቡ ተቃውሞ አቅራቢዎችን እረዳችኋለሁ፣ እሰማችኋለሁም ግን ግጭት አስከታዩ ሰልፍ ይቅርባችሁ ተውት ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡


በአንዳንድ ግዛቶች ሰልፈኞቹ ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ግጭት መግባታጋቸው ይነገራል፡፡


ፕሬዘዳንቱ ግን በጥሞና መነጋገሩን ብናስቀድም ይሻላል ብለዋል፡፡


እንደሚባለው በአሁኑ ወቅት ከናይጀሪያ መንግስታዊ ገቢ 70 በመቶ ያህሉ ለእዳ ክፍያ እየዋለ ነው፡፡


የየመን ሁቲዎች በኤደን ባህረ ሰላጤ በመተላለፍ ላይ በነበረች የንግድ መርከብ ላይ የሚሳየል ጥቃት ማድረሳቸው ተሰማ፡፡


ጥቃት የተሰነዘረባት የላይቤሪያን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበልብ እና የኮንቴይነሮች መጫኛ እንደሆነች አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡


መርከቧ የየትኛው አገር እና ኩባንያ እንደሆነች ግን በመረጃው አልተጠቀሰም፡፡


ሁቲዎቹ እስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻዋን ካላቆመች በቀጠናው በሚተላለፉ የተባባሪዎቿ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳችንን እንቀጥላለን በሚል አቋማቸው ገፍተውበታል፡፡


የየመን ሁቲዎች በመርከቦች ላይ የሚፈፅሙት ጥቃት ለ2 ሳምንታት ያህል ጋብ ብሎ መሰንበቱን መረጃው አስታውሷል፡፡


ሁቲዎቹ ጥቃት አድርሰንባታል ያሉት የንግድ መርከብ ስለደረሰባት ጉዳት የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡


የየመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ የኢራን ሁነኛ አጋሮች መሆናቸው ይነገራል፡፡



የተለያዩ አገሮች ዜጎቻቸው በአፋጣኝ ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ እየመከሩ እና እያስጠነቀቁ ነው ተባለ፡፡


ዜጎቻቸው ሊባኖስን በአፋጣኝ ለቀው እንዲወጡ ከጠየቁት መካከል አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ አውስትራሊያ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና ሳውዲ አረቢያ እንደሚገኙበት ቢቢሲ ፅፏል፡፡


እስራኤል ከሊባኖሱ የጦር ድርጅት (ሔዝቦላህ) ጋር ወደ ሙሉ ጦርነት ልትገባ ትችላለች የሚለው ስጋት አይሏል፡፡


ሔዝቦላህ በቅርቡ ለተገደለበት የጦር አዛዡ በቀል በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ጥቃት ለማድረስ እየዛተ ነው፡፡


በዚያ ላይ የሐማስ መሪ የነበሩት ኢስማየል ሐኒያ በቴሕራን መገደላቸው ኢራንንም ገዳይ ነች ያለቻትን እስራኤልን ለመበቀል አነሳስቷታል ይባላል፡፡


በቀጠናው የጦር ፍጥጫው እና ውጥረቱ ማየሉ ይነገራል፡፡


ሔዝቦላህ የኢራን ሁነኛ የጦር አጋር እና የፖለቲካ ሸሪክ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡



በዩጋንዳ M ፖክስ በተሰኘው የዝንጀሮዎች ፈንጣጣ የተያዙ 2 ሰዎች መገኘታቸው ተሰማ፡፡


በ M ፖክስ የተያዙት ሰዎች የተገኙ አገሪቱ ከጎረቤት ኮንጎ ኪንሻሣ በምትዋሰንበት የድንበር አቅራቢያ ባሉ ከተሞች እንደሆነ ዘ ኒው ታይምስ ፅፏል፡፡


የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታው በቀጠናው አገሮች እየተስፋፋ መምጣቱ ይነገራል፡፡


በኬኒያም ባለፈው ሳምንት በM ፖክስ በሽታ የተያዘ ሰው መለየቱን መረጃው አስታውሷል፡፡


ኮንጎ ኪንሻሣ ግን በሺህዎች የሚቆጠሩ የበሽታው ታጠቂዎች ያሉባት አገር ነች፡፡


በሽታው እንደ ሌሊት ወፍ ካሉ እንስሳት ወደ ሰዎች ይተላለፋል፡፡


ሀይለኛ ትኩሳት እና ራስ ምታት ፣ የጡንቻ መዛልና ሕመም እንዲሁም የሰውነት መጉረብረብ ከምልክቶቹ የተወሰኑት ናቸው፡፡


በበሽታው ከተያዙት የተወሰኑትንም እንደሚገድል ይነገራል፡፡


የኔነህ ከበደ

Comentarios


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page