በጋምቤላ ክልል ከ30 ያላነሱ ስደተኞች በረሃብና በምግብ እጦት እንዲሁም ምግብ ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ በደረሰባቸው ጥቃት መሞታቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተናገረ፡፡
30ዎቹ ሰዎች መሞታቸውን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ተወካዮች ነግረውኛል ሲል ኢሰማኮ በወጣው ሪፖርት አስረድቷል፡፡
ኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የስደተኞች እና ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱ በእጅጉ አሳስቦኛልም ብሏል፡፡
በቅርቡ ያደረኩት ክትትል የከፋ ሰብአዊ ሁኔታ እና የምግብ አቅርቦት እጥረትን በተለይም በስደተኞች ካምፖች ውስጥ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል ሲልም ተናግሯል።
ከነሐሴ ወር 2015 ጀምሮ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው የትጥቅ ግጭት እና ከጎረቤት ሀገራት ወደ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና ሶማሌ ክልሎች የሚገቡ ስደተኞች ሰብአዊ ፍላጎቱን የበለጠ እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል ሲል አስረድቷል።
በጋምቤላ ክልል ብቻ ወደ 400,000 የሚጠጉ ስደተኞች በተለያዩ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እንዳሉ የተናገረው ኮሚሽኑ በየመጠለያዎቹ ላሉት ስደተኞች ከሰኔ ወር ጀምሮ ምንም ዓይነት የምግብ እርዳታ አልተደረገም ብሏል።
በምግብ ዕርዳታ መቋረጥ ምክንያትም ከረሃብ ጋር ተያይዞ ለሞት የተዳረጉ መኖራቸውን ያስረዳው ኮሚሽኑ ቀድሞውንም ደካማ የነበረውን የስደተኞች እና የአስተናጋጅ ማህበረሰቡን ግንኙነት ችግሩ አናግቶታል ብሏል፡፡
በጋምቤላ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር የስደተኞችን ፈተና የበለጠ እንዳባባሰው አስረድቷል።
ስደተኞች ከካምፑ ውጭ ምግብ ፍለጋ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለጥቃት እንደሚጋለጡ እና በዚህም የተነሳ የበርካታ ስደተኞች ህይወት መጥፋቱን በሪፖርቱ አስረድቷል።
አንዳንድ ስደተኞች ከካምፑ ውጭ ምግብ ለማግኘት ማጭበርበር እና መስረቅን ውስጥ እንደሚሳተፉ የተናገረው ኢሰመኮ በዚህም ምክንያት ህይወት ያልፋል ብሏል፡፡
የምግብ ዕርዳታ መቆሙ እና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክያት ከ5 ዓመት በታች ያሉ ብቻ ሳይሆን ከ10 ዓመት በላይ የሆኑ ሕፃናትንም ለመቀንጨር እየተዳረጉ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
በጋምቤላ ክልል ከ30 ያላነሱ ስደተኞች በረሃብና በምግብ እጦት እንዲሁም ምግብ ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ በደረሰባቸው ጥቃት መሞታቸውን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ተወካዮች ንግረውኛል ሲልም ኢሰማኮ በሪፖርቱ አካቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከሰኔ 2014 እስከ ሰኔ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ የሚዳስሰውን ዓመታዊ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ሪፖርቱን ባወጣበት ወቅት የትጥቅ ግጭትና ግጭት ያስከተለው መፈናቀል ለእርሻ እና ተያያዥ ምርት ተግባራት እና ማህበራዊ አገልግሎቶች መቋረጥ ምክንያት እንደሚሆን አስታውሷል።
በኦሮሚያ ክልል እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በርካታ ወረዳዎች የተከሰተው ድርቅም የምግብ ዕርዳታ የሚሹ ሰዎችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል ብሏል።
በተለይ የሴቶች፣ ህጻናት እና አረጋውያን ተጋላጭነት በሪፖርቱ አጽንኦት የሰጠው ኢሰመኮ፤ የምግብ ዕርዳታና ሰብዓዊ ዕርዳታ በአስቸኳይ እንዲጀመር ሁሉም አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
ኮሚሽኑ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት እና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጨምሮ ከሚመለከታቸው ድርጅቶች ጋር በምግብ አቅርቦት መቋረጡ በተመለከተ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጉን ጠቅሶ ይህም የምግብ እርዳታ መቋረጥ በመላ ሀገሪቱ የስደተኞች ጥበቃ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረ አረጋግግጫለሁ ብሏል።
ኮሚሽኑ መንግስትና አለም አቀፍ አጋሮች የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የምግብ ዕርዳታውን እንደገና እንዲቀጥሉ ጠይቋል፡፡
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Kommentare