መስከረም 11፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- Sep 22, 2023
- 1 min read
በሊባኖሷ ርዕሰ ከተማ ቤይሩት በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ደጃፍ የጦር መሳሪያ መተኮሱ ተሰማ፡፡
በኤምባሲው ደጃፍ በተከፈተው ተኩስ ጉዳት የገጠመው ሰው የለም መባሉን አናዶሉ ፅፏል፡፡
በቤይሩት የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከፍተኛ ጥበቃ የማይለየው እንደሆነ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የተኩስ ከፋቹ ማንነት አልታወቀም ተብሏል፡፡
ተኩስ ከፋቹ በሌላት መኪና ወደ ቦታው በመምጣት ወደ ኤምባሲው በራፍ መተኮሱ ታውቋል፡፡
የሱዳን ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን በሌተና ጄኔራል ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ሀይል(RSF) በአለም አቀፍ ደረጃ በአሸባሪነት እንዲፈረጅላቸው ጠየቁ፡፡
አል ቡርሃን በአሸባሪነት እንዲፈረጅላቸው የጠየቁት ለተባበሩት መንግስታት 78ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር እንደሆነ TRT ዎርልድ ፅፏል፡፡
በሱዳን መንግስት ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ሀይል(RSF) መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰብአዊ ቀውሱን እያከፋ የመጣው ጦርነት ከ5 ወራት በላይ አስቆጥሯል፡፡
የፈጥኖ ደራሹ ሀይል አዛዥ በቪዲዮ ሊንክ (ምስለ ጉባኤ) አስተላለፉት በተባለ መልዕክት ሀይላቸው የተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል ተብሏል፡፡
የሱዳኑን ጦርነት ማስቆሚያ ተስፋ በቅርብ እንደማይታይ ዘገባው አስታውሷል፡፡
ለጦርነቱ ተባብሶ መቀጠል ተፋላሚዎቹ በአንተ ነህ፣ አንተ ነህ መካሰሳቸውን ቀጥለዋል፡፡
ዩክሬይን አሜሪካ ስሪቶቹን አብራምስ ታንኮች ልትረከብ ነው ተባለ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ታንኮቹ በመጪው ሳምንት ዩክሬይን እንደሚደርሱ ለሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ እንዳረጋገጡላቸው አናዶሉ ፅፏል፡፡
ዜሌንስኪ በዋይት ሐውስ ከፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ጋር መነጋገራቸው ተሰምቷል፡፡
ዩክሬይን ከሩሲያ ጋር የማካሂደውን ጦርነት በድል አድራጊነት እንድወጣው ታንኮቹ በእጅጉ ያግዙኛል ስትል ቆይታለች፡፡
አሜሪካ በአሁኑ ወቅት የ325 ሚሊዮን ዶላር የዋጋ ግምት ያላቸውን የጦር መሳሪያዎች ለዩክሬይን ለማቅረብ መሰናዳቷን ባይደን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና በአሜሪካ ኮንግረስ ሪፖብሊካውያን እንደራሴዎች ዘንድ ለዩክሬይን በሚቀርበው የጦር ድጋፍ ጉዳይ ተቃውሞ እያቆጠቆጠ መምጣቱ ተሰምቷል፡፡
ዩክሬይን ከሩሲያ ጋር ውጊያ ከገጠመች ከአመት ከመንፈቅ በላይ እንደሆናት ዘገባው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
###Abrams_Tanks ###RSF ##
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments