top of page

መስከረም 14፣2017 - የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ለመቅረፍ አምርቶ ቢያቀርብም ምርቱ ፈላጊ ማጣቱን መንግስታዊው የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ተናገረ

ገበያው ላይ ያለውን የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ለመቅረፍ አምርቶ ቢያቀርብም ምርቱ ፈላጊ ማጣቱን መንግስታዊው የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ተናገረ፡፡


ወቅቱ የትምህርት መጀመሪያ እንደመሆኑ የመማሪያ ቁሳቁሶች ዋጋ አልቀመስ እያለ ነው፡፡


በተለይም የመማሪያ ደብተር እጥረት አለ ዋጋውም ከወትሮው በተለየ ከፍ ብሎ ታይቷል፡፡


ለመማሪያ የሚሆን ደብተር በገበያው ላይ ካለው ዋጋ እስከ 20 በመቶ ቅናሽ በማድረግ እያቀረብኩ ነው የሚለው ድርጅቱ ምርቱን የሚረከበው ማጣቱን ነግሮናል፡፡


የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ደሳለኝ እንደሚሉት ድርጅቱ በትምህርት ዘርፍ ያሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ልሆኑ ድርጅቶች በሚያቀርቡት የይመረትልኝ ጥያቄ መሰረት ሁሉንም አይነት የትምርት መሳሪያዎች እያመረተ ያቀርባል፡፡


በቅርቡ በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት የወረቀት ዋጋ በመወደዱ በሃገር ውስጥ የሚመረተውም ከውጭ የሚገባውም ደብተር ዋጋ ጨምሯል፡፡


ድርጅቱ ግን ከማሻሻያው ቀድሞ ያስገባው የማምረቻ ግብዓት በመኖሩ በድርጅቶች ከታዘዘው በተጨማሪ 200ሺህ ደብተር በማምረት በአዲስ አበባ፣ በሃዋሳ እና በባህርዳር ባሉት የሽያጭ ማዕከሎቹ ያለ ምንም የዋጋ ጭማሪ አንድ ደብተር በ45 ብር ዋጋ እየሸጨ ነው፤ በገበያ ላይ ያለው የአንድ ደብተር ዋጋ እስከ 60 ብር ይደርሳልም ብለዋል፡፡


ከተሰራጨው ባሻገር ተጨማሪ 100 ሺህ ደብተሮች ህትመት ላይ መሆናቸውንና ካለው ፍላጎት አንፃር በፃም ጥቂት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ያሬድ በሽያጭ የምናቀርበውን ግን ገዢ እገኘን አይደለም፤ ገዢው ከሃገር ውስጡ ይልቅ ከውጭ የሚገቡትን መግዛት ይመርጣል ይላሉ፡፡


በትምህርት ሚኒስቴር ለተማሪዎች ከሚሰራጩ የመማሪያ መፅሃፍት 60 በመቶውን ህትመት የሚከውነው የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ላለንበት የ2017 የትምህርት ዘመን 500,000 የመፅሃፍት ህትመት መከወኑን ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡


ድርጅቱ በሽሮ ሜዳ፣ በ4ኪሎ፣ ጉርድ ሾላ በባህርዳር እና በሃዋሳ ባሉት መሸጫ ሱቆቹ በተለይ ደብተሮችንና ሌላውንም በማቅረብ በገበያው ላይ ያለውን የዋጋ ውድነት ለማረጋጋት የበኩሉን እተወጣ መሆኑንም ተናግሯል፡፡



ምንታምር ፀጋው

Comentários


bottom of page