top of page

መስከረም 2፣2017 - በአዲስ አበባ ከበዓሉ ዋዜማ እስከ ዛሬ መስከረም 2፣2017 ዓ.ም ባሉት ቀናት በትራፊክ አደጋ የ6 ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡

የ2017 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል እንዴት አለፈ ስንል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ጠይቀናል፡፡


የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ በሰጡን ምላሽ ከዋዜማው ጀምሮ በተከሰቱት የትራፊክ አደጋዎች የ4 ሴቶችና የ2 ወንዶች ሰዎች ይህወት አልፏል ብለዋል፡፡


በዚህም በበዓሉ ዋዜማ ጳጉሜ 5 ቀን በጉለሌ ክፍለ ወረዳ 6 ቀለበት መንገድ አካባቢ በደረሰ የትራፊክ አደጋ አንድ የ35 ዓመት ግለሰብ ህይወቱ አልፏል፡፡


ትናንት በበዓሉ እለት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቀይ አፈር እየተባለ በሚጠራዉ አካባቢ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ መንገድ ሲሻገሩ የነበሩ ሶስት ሴቶችን በመግጨት አደጋ አድርሷል፣ ተጎጂዎቹም ህይወታቸዉ ወዲያውኑ አልፏል ብለውናል።


ከሟቾቹ ጋር አብራ የነበረችና አንዲት እራሷን የሳተች ሴት በእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አምቡላንስ ወደ ጤና ተቋም ተወስዳለች።



በተመሳሳይ ትላንት ምሽት 2 ሰዓት ገደማ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስቴዲየም አካባቢ ከመስቀል አደባባይ ወደ ሜክሲኮ ሲጓዝ የነበረ ተሸከርካሪ መንገድ በማቋረጥ ላይ የነበሩ የ50 ዓመት ሴት በመግጨቱ በደረሰው አደጋ ተሞት ዳርጓቸዋል፡፡


በዛሬው እለትም እንዲሁ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቄራ አካባቢ በተመሳሳይ መንገድ ሲያቋርጥ የነበረ የ44 ዓመት ግለሰብ ከሳርቤት ወደ ቄራ ሲጓዝ በነበረ ተሸከርካሪ ተገጭቶ ይህወቱ ማለፉንም ነግረውናል፡፡


አደጋውን ያደረሱ ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንና የአደጋዉ መንስኤ በፖሊስ እየተጠራ መሆኑን ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ጠቁመዋል።


በሌላ በኩል በከተማዋ በበዓሉ ዋዜማም ሆነ በበዓሉ ዕለት ምንም ዓይነት የእሳት አደጋ እንዳላጋጠመ የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ ነግረውናል።


ከአዲስ ዓመት በኋላም የመስከረም ወር በዓላት ተከታትለው የሚመጡበት በመሆኑ አክባሪዎች በሙሉ በዓሉን ለማክበር በሚኖረው ጥድፊያ ከሚፈጠሩ ስህተቶች ሊጠነቀቅ ይገባል ሲነ,ሉም አሳስበዋል፡፡


በ2016 ዓ.ም በተከበሩ በሁሉም በዓላት ቀላል አደጋዎች ካልሆነ በስተቀር የሚጠቀስ አደጋ እንዳልነበር ከአቶ ንጋቱ ሰምተናል።


ሙሉ ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ ይህንን ማስፈንጠሪያን ይጫኑ... https://tinyurl.com/346ms2j5


ምንታምር ፀጋው

Comments


bottom of page