top of page

መስከረም 23፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች



በሩዋንዳው የዘር ፍጅት ተዋናይ ነበር የተባለ የቀድሞ የጦር መኮንን ኔዘርላንድ ውስጥ ተይዞ መታሰሩ ተሰማ፡፡


በዘር ፍጅቱ ተጠርጥሮ የተያዘው የቀድሞ የጦር መኮንን ፒየር ክሌቨር ክራንግዋ የተባለ ግለሰብ እንደሆነ የኔዘርላንድስ አቃቢያነ ህግ ተናግረዋል፡፡


ግለሰቡ በዘር ፍጅቱ ዘመን በሩዋንዳዋ ርዕሰ ከተማ ኪጋሊ አቅራቢያ በ30 ሺህ ያህል ሰዎች ላይ በተፈፀመ እልቂት ሲፈለግ የቆየ ነው ተብሏል፡፡

የሩዋንዳ መንግስት ከ11 ዓመታት በፊት ግለሰቡ ተላልፎ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡


በሩዋንዳ ከ30 ዓመታት ገደማ በፊት በተፈፀመው የዘር ፍጅት አብዛኞቹ ቱትሲዎች የሆኑ ከ800 ሺህ ያላነሱ ሰዎች ማለቃቸው ይነገራል፡፡



የኮንጎ ኪንሻሣው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊው ዶክተር ዴኒስ ሙክዌጌ በአገሪቱ በሚካሄደው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ሊፎካከሩ ነው፡፡


ዶክተር ሙክዌጌ እጩነቴን እወቁልኝ ማለታቸውን ዘ ኢስት አፍሪካን ፅፏል፡፡


ዶክተር ዴኒስ ሙክዌጌ በጦር ቀጠና የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ለተፈፀመባቸው ሴቶች በመርዳት ባደረጉት የጤና ድጋፍ በማድረግ ከ5 ዓመታት በፊት የኖቤል የሰላም ሽልማትን እንዳሸነፉ ዘገባው አስታውሷል፡፡

ፕሬዘዳንት ፊሊክስ ሲሼኬዲም በድጋሚ ለመመረጥ እንደሚፎካከሩ እወቁልኝ ያሉት ሰሞኑን ነው፡፡


በኮንጎ ኪንሻሣ ምርጫው ከ3 ወራት ባልበለጠ ጊዜ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡


ምርጫው የሚካሄደው በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ነባሩ የፀጥታ መደፍረስ ባልተሻሻለበት አጋጣሚ እንደሆነ ዘገባው አስታውሷል፡፡




የኬንያ መንግስት የፀጥታው ምክር ቤት በሔይቲ አለም አቀፍ ህግ እና ሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲሰማራ መወሰኑን በእጅጉ አወደሰው፡፡


ኬንያ ወደ ካሪቢያኗ አገር 1 ሺህ የፖሊስ ባልደረቦችን አሰማራለሁ ስትል መቆየቷን አናዶሉ አስታውሷል፡፡


ምስራቅ አፍሪካዊቱ አገር የፀጥታውን ምክር ቤት ውሳኔ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ አማካይነት እሰየው ማለቷ ተሰምቷል፡፡


በሔይቲ የሚሰማራውን አለም አቀፍ ህግ እና ሥርዓት አስከባሪ ሀይል ኬኒያ እንደምትመራው ታውቋል፡፡


ሔይቲ በተደራጁ የወሮበሎች ቡድኖች አበሳዋን እያየች እና ታላቅ ሥርዓተ አልበኝነት እንደነገሰባት ዘገባው አስታውሷል፡፡




የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው የቆዩት ኬቪን ማካርቲ ከሀላፊነታቸው ተባረሩ፡፡


ሪፖብሊካዊው የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ከሀላፊነት የተባረሩት ሌላኛው ሪፖብሊካዊ የፍሎሪዳ እንደራሴ ማት ጋኤትዝ ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ መሰረት በተሰጠ ድምፅ እንደሆነ ኒውስ 18 ፅፏል፡፡


ማት ጋኤትስ የውሳኔ ሀሳቡን ያቀረቡት ኬቪን ማካርቲ ለዩክሬይን የእርዳታ ገንዘብ እንዲሰጥ ከዋይት ሐውስ አስተዳደር ጋር በሚስጥር ተደራድረዋል ብለው እንደሆነ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

ኬቪን ማካርቲ ግን ከዋይት ሐውስ ጋር በሚስጥር ተደራድረዋል መባሉን አላደረኩትም ባይ ናቸው፡፡


በውሳኔ ሐሳቡ ላይ በተሰጠ ድምፅ የህዝብ ተወካዮቹ ምክር ቤት 216 ለ210 በሆነ የድምፅ ልዩነት ማካርቲ ከአፈ ጉባኤነታቸው እንዲነሱ መወሰኑ ተሰምቷል፡፡


በአሜሪካ ታሪክም በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ከአፈ ጉባኤነቱ ሀላፊነት በመባረር ማካርቲ የመጀመሪያው ሆነዋል ተብሏል፡፡


ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ በአጣዳፊ ቋሚ አፈ ጉባኤ እንደሚሰይም ተስፋ አደርጋለሁ ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡



የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comentarios


bottom of page