በኢትዮዽያ አስፈላጊ የጉዞ መረጃ ላላቸው የግል ተጓዦች እስከ 5,000 የአሜሪካን ዶላር፣ ለንግድ ሥራ ተጓዦች ደግሞ እስከ 10,000 የአሜሪካን ዶላር በጥሬ ገንዘብ መሸጥ የሚችሉ አምስት የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ስራ ሊጀምሩ መሆኑ ተሰማ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለ5 ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የስራ ፈቃድ መስጠቱን ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትን ለማስፋፋትና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍ ለማድረግ ነው ይህን ፍቃድ መስጠቱ የተነገረው።
አሁን በሥራ ላይ ካሉት ከባንክ ጋር ከተያያዙ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በተጨማሪ ከባንክ ጋር ዝምድና የሌላቸው የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችን ለመክፈት የሚያስችል (NBE Foreign Exchange Directive No. FXD/01/2024) መመሪያ መውጣቱ ይታወሳል።
በዚሁ መሠረት አምስት የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ተፈላጊውን መስፈርት ማሟላታቸው ተረጋግጦ የሥራ ፈቃድ ጨብጠዋል ተብሏል።
ፍቃድ ካገኙ ድርጅቶች፦
1. Ethio Independent Foreign Exchange Bureau
2. Dugda Fidelity Investment PLC
3. Global Independent Foreign Exchange Bureau
4. Robust Independent Foreign Exchange Bureau
5. Yoga Forex Bureau መሆናቸው ተረጋግጧል።
የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በሙሉ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ሀገር ጥሬ ገንዘቦችን በመግዛትና በመሸጥ ስራ ይሳተፋሉ ተብሏል።
ከባንኮች ጋር በመቀናጀትም ለወጪና ገቢ ንግድ የሚውል የውጭ ምንዛሪ እንደሚያመቻቹ ተሰምቷል።
የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገበያ ለማስፋፋትና ለማዳበር እንደሚያግዙም ብሔራዊ ባንክ ተናግሯል።
የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በዋናነት የሚያካሂዱት የውጭ ምንዛሪ ሽያጭም ሆነ ግዥ ወዲያውኑ የሚፈጸም (spot transaction) ብቻ እንደሚሆን ተሰምቷል።
የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ያለ ጉምሩክ ዴክላራሲዮን ከደንበኞች እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር፤ የጉምሩክ ፈቃድ ከሚያቀርቡት ደግሞ ከዚያ በላይ የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ መግዛት ይችላሉ፡እንደሚችሉ ታውቋል።
እንዲሁም ተፈላጊ የጉዞ መረጃ ላላቸው የግል ተጓዦች እስክ 5,000 የአሜሪካን ዶላር፣ ለንግድ ሥራ ተጓዦች ደግሞ እስከ 10,000 የአሜሪካን ዶላር በጥሬ ገንዘብ መሸጥ እንደሚችሉ ተረጋግጧል።
የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎቹ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጡ የአሠራር፣ የደህንነት፣ የሪፖርት አደራረግና የመዝገብ አያያዝ መስፈርቶችን በአግባቡ ተግባራዊ ስለማድረጋቸው ባንኩ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን ተናግሯል።
ተህቦ ንጉሴ
Comments