መስከረም 29፣2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- Oct 9, 2024
- 2 min read
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ሊባኖሳዊያን ሔዝቦላህን መንግለው እንዲጥሉት ጥሪ አቀረቡ፡፡
ኔታንያሁ የሊባኖስ ሕዝብ ሔዝቦላህን መንግሎ ካልጣለው አገሪቱ እንደ ጋዛ ትፈራርሳለች ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ማስጠንቀቂያውን የሰጡት በቀጥታ ለሊባኖስ ህዝብ እንዲደርስ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡
እስራኤል በሊባኖስ የአየር ጥቃቷን እና በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የየብስ ዘመቻዋን አድማስ እያሰፋች ነው፡፡
በ2 ሳምንታት ጊዜ በእስራኤል የሊባኖስ ጥቃት 1 ሺህ 400 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል፡፡
1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
የኔታንያሁ ማስጠንቀቂያ ገና የከፋው እንደሚመጣ የሚጠቁም ነው ተብሏል፡፡

በኮንጎ ኪንሻሣ የቀጠለው ውስብስብ ጦርነት ባለፉት 9 ወራት አንድ ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል ተባለ፡፡
የኮንጎ ኪንሻሣ ምስራቃዊ ክፍል በትጥቅ አመፅ እና በጦርነት መታመስ ከያዘ በርካታ አመታትን አስቆጥሯል፡፡
ከ100 ያላነሱ አማጺ እና የታጠቁ ቡድኖች መርመስመሻ ነው ይባላል፡፡
ባለፉት 9 ወራት 1 ሚሊዮን ያህል ሰላማዊ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዳፈናቀለ የተናገሩት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ምክር ቤት የበላይ ቮልከር ተርክ እንደሆኑ TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡
የምስራቃዊ ኮንጎ ኪንሻሣ ቀውስ ያለ ሁነኛ መፍትሄ እንደዘለቀ መረጃው አስታውሷል፡፡
የሩሲያ ጦር በምስራቃዊ ዩክሬይን ቶሬትስክ ወደተባለችዋ ከተማ እየተጠጋ ነው ተባለ፡፡
እንዳውም በተወሰኑ አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ እየዘለቀ ነው መባሉን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
የዩክሬይን የጦር ሹሞችም ከተማዋን በሩሲያ ሀይሎች ላለማስነጠቅ ውጊያ እየተካሄደ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ከተማዋ በሉሃንስክ ግዛት የምትገኝ ነች ተብሏል፡፡
ቶሬትስክ ወታደራዊ ፋይዳዋ የጎላ እንደሆነ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
ቀደም ሲል የሩሲያ ጦር በዳኔስክ ግዛት ቀስ በቀስ ብዙ ከተሞችን በእጁ ማስገባቱ ለትውስታ ተነስቷል፡፡
የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪየር ስታርመር ለእስራኤል ሁሉንም ዓይነት የጦር መሳሪያዎች መሸጥ አናቆምም አሉ፡፡
ቀደም ሲል የብሪታንያ መንግስት ለእስራኤል በሽያጭ ሲያቀርባቸው ከነበሩ የጦር መሳሪያዎች የ30 ዓይነቶቹን የሽያጭ ፈቃድ መሰረዙን አረብ ኒውስ አስታውሷል፡፡
ሆኖም የተወሰኑ እንደራሴዎች የብሪታንያ መንግስት ሁሉም ዓይነት የጦር መሳሪያዎች በሽያጭ ለእስራኤል እንዳይሰጡ ግፊት እያደረጉ ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው ተጠርተው ምላሽ መስጠታቸው ተሰምቷል፡፡
ሁሉንም ዓይነት የጦር መሳሪያዎች ለእስራኤል እንዳይሸጥ ማድረግ አንችልም ብለዋል፡፡
ኬየር ስታርመር እንደዛ በማድረግ የእስራኤልን ራሷን የመከላከል አቅሟን ልናዳክም አይገባም የሚል ምላሽ መስጠታቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
Comments