በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግስታት መካከል ያለው ግንኙነት እንደቀድሞ በሰላማዊ ትብብርና ግንኙነት መንፈስ እንደቀጠለ ነው ምንም አዲስ ነገር የለም ተባለ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት ሀላፊ አምባሳደር ነቢያት በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በሰጡት መግለጫቸው ስለ ኢትዮ ኤርትራ ወቅታዊ ግንኙነት ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት እንደ በፊቱ ቀጥሏል ምንም የተለወጠ ነገር የለም ሲሉ መልሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰብአዊ መብቶች ካውንስል አባል እንድትሆን ለሶስተኛው ጊዜ መመረጧንም አምባሳደር ነቢያት ተናግረዋል፡፡
በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎችን በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በቤይሩት በችግር ውስጥ ያሉ ሁሉንም ዜጎችን የማስወጣት ስራ ለመስራት የመኖሪያ ፈቃድ ያለውና የሌለው ብሎ ሳይለይ ወደ ሀገር ለመመለስ የፈቀዱ ኢትዮጵያዊንን እየመዘገበ ነው፡፡
ይሁንና ከዛሬ ነገ በሊባኖስ ያለው ሁኔታ ይሻሻላል በሚል የሚመዘገበው ዜጋ እያመነታ በመሆኑ በበቂ መጠን ምዝገባ እየተካሄደ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ዜጎች ወደ ሀገር ለመመለስ ምዝገባ ሲደረግ ገንዘብ እንዲከፍሉ እየተጠየቁ ነው ይህ ለምን ሆነ ተብለው የተጠየቁት አምባሳደር ነቢያት፤ እስከሚያውቁት ድረስ ምንም ዓይነት የገንዘብ ክፍያ እንዳልተጠየቀ ይሁንና የነገሩን እውነት ለማጣራት የበለጠ መረጃ መሰብሰብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የኔነህ ሲሳይ
コメント