top of page

መጋቢት 11፣2016 - ከፕሮጀክቶች ካሳ ጋር የተያያዙ ክሶች ክርክር የሚደረገው በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ብቻ ይሆናል ተባለ

በክልሎችም ሆነ በከተማ አስተዳደሮች የፌዴራል መንግስት የሚገነባቸው ፕሮጀክቶች በተመለከተ ከልማት ተነሺ ካሳ ጋር የተያያዙ ክሶች ክርክር የሚደረገው በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ብቻ ይሆናል ተባለ፡፡


ተሻሽሎ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በቀረበው ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን፣ ካሣ የሚከፈልበትን እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ የሚመለከተው ረቂቅ አዋጅ፤ የፍርድ ቤት ክርክሮች በፌዴራል ፍርድ ቤት ብቻ እንዲሆን የሚደነግግ ነው፡፡


እንደ መንገድ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የኤልክትሪክና መሰል ስራዎች በፌዴራል መንግስት ተቋም ስለሚገነቡ ፕሮጀክቱ የሚተገበረው በክልል ቢሆንም ቅሬታ ያለው ሰው በፍርድ ቤት መከራከር ከፈለገ በፌዴራል ፍርድ ቤት ብቻ እንዲሆን ህጉ ያስገድዳል፡፡


ከዚህ ቀደም በነበረው ፕሮጀክቶቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ባሉ ፍርድ ቤቶች ክርክር ማድረግ ይቻል የነበረ ሲሆን በአዲሱ ረቂቅ ሃላፊነቱ ለፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ተሰጥቷል፡፡


በዚህም ምክንያት ከንብረት ካሣ፣ ከልማት ተነሺዎች ድጋፍ ከኢኮኖሚ ጉዳት ካሣ፣ የማህበራዊ ትስስር መቋረጥ እና የስነ ልቦና ጉዳት ካሣ ጋር ተያይዞ በፍርድ ቤት መከራከር የሚፈልጉትን ሁሉ ካሉበት ክልል ወደ ፌዴራል መጥተው አቤት እንዲሉ በረቂቁ ተደንግጓል፡፡


በተጨማሪም በተለይ በፍርድ ቤት ከሚደረጉ ክርክሮች ጋር በተያያዘ በፍርድ ቤቶች የሚሰጡ ጊዜያዊ ትዕዛዝም ከፍርድ ቤቱ ፕሬዘዳንት እውቅና ውጭ ተፈፃሚ መሆን አይችሉም ተብሏል፡፡


በተለይ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የፌዴራል መንግስት ተቋምን የባንክ ሂሳብ የማገድ ወይም ከአፈፃፀም ጋር በተያያዘ ከፍተኛ አመራሮች ተገደው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የሚሰጡ የፍርድ ቤት ትዕዛዞች ከፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት እውቅና ሳይሰጡ ተፈፃሚ እንደማይሆን ከረቂቅ አዋጁ ላይ ተመልክተናል፡፡


ትዕግስት ዘሪሁን


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


bottom of page