የአውሮፓ ህብረት አባሎች በየአገሮቻቸው ታግዶ የሚገኝን የሩሲያ ገንዘብ ለዩክሬይን የጦር መሳሪያ መግዣ ሊያውሉት ነው ተባለ፡፡
በጉዳዩ ላይ የህብረቱ አባል አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ነገ ተሰብስበው እንደሚመክሩበት አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
በአውሮፓ ህብረት አባል አገሮች ታግዶ የሚገኘው የሩሲያ ገንዘብ 200 ቢሊዮን ዩሮ ያህል እንደሆነ ይገመታል፡፡
የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ጆሴፍ ቦሬል ታግዶ የሚገኘውን የሩሲያ ገንዘብ ለዩክሬይን የጦር መሳሪያ መግዣ ማዋላችን አይቀሬ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ዩክሬይን በአሁኑ ወቅት የጦር መሳሪያ እና የተተኳሾች እጥረት እንደገጠማት ይነገራል፡፡
የኬንያ ሰራተኞች ለድሆች እና ባለዝቅተኛ ገቢዎች ቤት መገንቢያ የ 1.5 በመቶ ተጨማሪ ግብር ሊከፍሉ ነው፡፡
ፕሬዘዳንት ዊሊያም ሩቶ ሕጉ ስራ ላይ እንዲውል ፊርማቸውን እንዳኖሩበት ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ከተጨማሪ የግብር ክፍያው የሚሰበሰበው ገቢ ለድሃ እና ባለ ዝቅተኛ ገቢ ኬንያውያን የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ይውላል ተብሏል፡፡
ይሁንና አዲሱ የግብር ክፍያ በተቃዋሚዎች እና በብዙ ግብር ከፋዮች እየተነቀፈ መሆኑ ታውቋል፡፡
ይሁንና ይሄ የግብር ዓይነት መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ ከሚገኙ ሰራተኞች እንዴት እንደሚሰበሰብ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም፡፡
የቤት መገንቢያውን ገንዘብ የሚያስተዳድር መስሪያ ቤት እንደሚቋቋም ተጠቅሷል፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት የየመን ሁቲዎች በቀይ ባህር ተላላፊ መርከቦች ላይ የሚፈፅሙትን ጥቃት ያለ አንዳች መዘግየት እንዲያቆሙ ጠየቃቸው፡፡
ድርጊታቸውንም እንዳወገዘው አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡
ሁቲዎቹ እስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻዋን ካላቆመች በተባባሪዎቿ መርከቦች ላይ ጥቃታችንን አናቆምም ባዮች ናቸው፡፡
መርከብ መትተው እስከ ማስጠም ደርሰዋል፡፡
ምክር ቤቱ ቀደም ሲል የሁቲዎቹ ጥቃት እንዲቆም ውሳኔ ማሳለፉን ዘገባው አስታውሷል፡፡
ሁቲዎቹ የምክር ቤቱን ውሳኔ እንዲያከብሩ ተጠይቀዋል፡፡
የቀይ ባህሩ ቀውስ ያለ ሁነኛ መፍትሄ እንደዘለቀ ነው ተብሏል፡፡
የየመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ የኢራን ሁነኛ የጦር እና የፖለቲካ አጋሮች ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡
የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ አፈ ጉባኤው ኖሶቪዌ ማፒሣ ንካኩላ መኖሪያ ቤት በአገሪቱ ልዩ ፖሊስ መፈተሸ ተሰማ፡፡
የአፈ ጉባኤዋ የጆሃንስበርግ መኖሪያ ቤት የተበረበረው የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ፈፅመውታል በተባለው ምዝበራ ምክንያት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ንካኩላ የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ባልተገባ ሁኔታ ለተሰጠ መንግስታዊ ኮንትራት ጉቦ ተቀብለዋል ተብለው ስማቸው በክፉ እየተነሳ መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ፖሊስ በመኖሪያ ቤታቸው ብርበራ ያደረገው በአቃቤ ህግ ጥያቄ መሰረት ነው ተብሏል፡፡
ንካኩላ የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት አንድ የትራንስፖርት ኩባንያ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን እንዲያጓጉዝ ባልተገባ ሁኔታ ጨረታውን እንዲያሸንፍ ላደረጉበት የ120 ሺህ ዶላር ጉቦ ተቀብለዋል እየተባለ ነው፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments