በአሜሪካ ባልቲሞር ከተማ የሚገኘው የፍራንሲስ ስኮት ድልድይ ተደረመሰ፡፡
በፓታፔስኮ ወንዝ ላይ የተዘረጋው ትልቅ ድልድይ የተደረመሰው ምሰሶው በተላላፊ መርከብ ከተመታ በኋላ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ከ20 የማያንሱ መኪኖች ወንዙ ውስጥ መውደቃቸው ተሰምቷል፡፡
ዝርዝሩ ባይታወቅም ጉዳት የገጠማቸው ሰዎች እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡
የመርከቧ ባሕረኞች ግን አንዳችም ክፉ አልገጠማቸውም ተብሏል፡፡
የነፍስ አድን ጥረቱ መቀጠሉ ተሰምቷል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ዋነኛው የተቃዋሚዎች የፖለቲካ ማህበር ዴሞክራቲክ አሊያንስ ከምርጫው በኋላ ከአሁኑ ገዢ የፖለቲካ ማህበር /ANC/ ጋር በጥምር መንግስት ምስረታ ጉዳይ ሊደራደር እንደሚችል ፍንጭ ሰጠ፡፡
በአገሪቱ አዲስ የተቋቋመው MK የፖለቲካ ማህበር የ ANCን ድምፅ ሊሻማው እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በዚህ በፓርላማው ANC አብላጫነቱን ሊያጣ ይችላል ተብሏል፡፡
MK የተቋቋመው ከገዢው ANC ባፈነገጡት በቀድሞው ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ እንደሆነ ይነገራል፡፡
MK የፖለቲካ ማህበር ANCን በከባዱ መቀናቀኑ አይቀርም መባሉን ሬውተርስ ፅፏል፡፡
የህዝብ አስተያየት መለኪያዎችም የ ANC ድጋፍ መሳሳቱን እንደሚያሳዩ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት ወር እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዘለታል፡፡
እስራኤል እና የፍልስጤማውያ የጦር ድርጅት (ሐማስ) በፀጥታው ምክር ቤት የተኩስ አቁም ውሳኔ አቋማቸው ለየቅል ነው ተባለ፡፡
የምክር ቤቱ ውሳኔ ከአጣዳፊው የተኩስ አቁም በተጨማሪ ታጋቾች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ጭምር እንደሚጠይቅ ሬውተርስ ፅፏል፡፡
ሐማስ የተኩስ አቁም ውሳኔውን በእጅጉ እደግፈዋለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
ታጋቾችንም እስራኤል በያዘቻቸው ፍልስጤማውያን እስረኞች ለመቀያየር ዝግጁ ነኝ ብሏል፡፡
አሜሪካ ድምፀ ተአቅቦ በማድረጓ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ዋይት ሐውስ ከቀዳሚ አቋሙ ተንሸራትቷል ሲሉ ነቅፈዋል፡፡
የዋይት ሐውስ አስተዳደር ግን በእስራኤል ድጋፋችን ላይ ያደረግነው ለውጥ የለም በማለት ላይ ይገኛል፡፡
የሞዛምቢክ መንግስት ሰራዊት ከፅንፈኛ ታጣቂዎች ጋር በሚያደርገው ትንቅንቅ እየረዳው የሚገኘው የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ /ሳድክ/ አባል አገሮች ጦር ሊወጣ ነው ተባለ፡፡
የሳድክ አባል አገሮች ጦር ከሞዛምቢክ የሚወጣው ወታደራዊ ተግባራቱን ለማከናወን የገንዘብ እጥረት ስለገጠመው እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የሳድክ ጦር ምናልባትም እስከ ሐምሌ ባሉት ወራት ከሞዛምቢክ ጠቅልሎ እንደሚወጣ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡
የሞዛምቢኩ ፕሬዘዳንት ፊሊፔ ኒውሲ የሳድክ ጦር ወጣ ማለት ፅንፈኞችን መውጋታችንን እናቆማለን ማለት አይደለም ብለዋል፡፡
ሩዋንዳም ከ2 ሺህ በላይ ወታደሮቿን በመላክ የሞዛምቢክን ጦር ስታግዝ መቆየቷን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comentários