top of page

መጋቢት 19 2017 - የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የምግብ በጀት በአራት ዕጥፍ ጨምሮ እንዲሻሻል መደረጉና የወጪ መጋራት (Cost Sharing) ላይ የሚጨመረው ክፍያ

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የምግብ በጀት በአራት ዕጥፍ ጨምሮ እንዲሻሻል መደረጉ ይታወሳል፡፡


ይህ በየጊዜው እንዲሻሻል ሲጠየቅ የነበረው የምግብ በጀት መሻሻሉ መልካም ሆኖ እያለ የምግብ በጀት ተመን በጨመረው ልክ የወጪ መጋራት ( #Cost_Sharing ) ላይ የሚጨመረው ክፍያ በሌላ በኩል ስጋት እንደፈጠረባቸው ተማሪዎች ነግረውናል፡፡


ለአብነትም በአዲሱ የምግብ ሜኑ ስሌት መሰረት እስከ 6 ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ያለው ትምህርት የወሰደ ተማሪ፤ ተመርቆ ሲወጣ ዋናውን የትምህርት ማስረጃ ለማግኘት ለመንግስት 150,000 ብር ገደማ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡

ይህ መሆኑ በሀገሪቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ለተመራቂዎቹ ከባድ እንደሆ የተጠቆመ ሲሆን ለዚህም መንግስት ሌሎች አማራጮችን እንደመፍትሄ ሊያይ ይገባልም ሲሉ የዘርፉ ባለሞያዎች መክረዋል፡፡


ከዚህ ጋር ተያይዞ እንደ አንድ የመፍትሄ ሀሳብ በባለሙያዎች ሲቀርብ የሚሰማው ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ስለቀነሰ መንግስት መደጎም አይችልም ወይ የሚለው ነው፡፡


ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳዳር እና የመሰረተ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ ሰለሞን አብረሃ(ዶ/ር) ወደ ዩኒቨርሲቲ በቀጥታ አልፎ የሚገባው ተማሪ ቁጥር ይቀንስ እንጂ፤ በአቅም ማሻሻያ የሚገባ ተማሪ ተደምሮ ከበፊቱ በጣም የራቀ የሚባል አይደለም ዩኒቨርሲቲዎች የሚቀበሉት ብለውናል፡፡

ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ላይ የተማሪዎች የቀን የምግብ በጀት ከነበረበት 22 ብር ወደ 100 ብር ከፍ እንዲል ከመደረጉም ባሻገር፤ በሁሉም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የምግብ ዝርዝር ወጥ እንዲሆን ትምህርት ሚኒስቴር ለዩኒቨርሲቲዎች ደብዳቤ ጽፎ ነበረ፡፡


ይሁን እንጂ ይህ መመሪያ ከወረደ እና የምግብ በጀት ተመኑ ከተሻሻለም በኋላ በነበረው የምግብ ዝርዝር መሰረት የቀጠሉ ዩኒቨርሲቲዎች መኖራቸውን ሰምተናል፡፡


መላኩ ይርጋለም በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የ5 ዓመት የህግ ተማሪ እና በዩኒቨርሲቲው የተማዎች ህብረት የማህበራት እና የክበባት ተጠሪ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የምግብ አቅርቦት ላይ ማሻሻያ ቢኖረውም ትምህርት ሚኒስቴር ያወረደው የምግብ ዝርዝር መመሪያ ግን ተግባራዊ እንዳልተደረገ ነግሮናል፡፡

በተማሪዎች ጥያቄ መሰረት የተማሪዎች ህብረቱ ስለ ጉዳዩ ለዩኒቨርሲው አመራሮች ሲጠይቅ በክልሉ ያለው አለመረጋጋት እንደ አንድ ምክንያት እንደሚጠቀስ ከተማሪ ምላኩ ሰምተናል፡፡ በተለይም እንደነ አትክልት ያሉ በመመሪያው የተጠቀሱት የምግብ ዝርዝሮች በአካባቢው እንደልብ ከማይገኙ መካከል መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡


ይህን የተማሪዎች ጥያቄ ያነሳንላቸው በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳዳር እና የመሰረተ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚው ሰለሞን አብረሃ(ዶ/ር) ፤ መመሪያው ከወረደ ጥቂት ወራት ነው፤ ስካሁን ባለው ጊዜ ወርደን የመመሪያውን አፈጻፀም አልተመከትንም ብለውናል፡፡ ነግር ግን በቅርቡ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ተወርዶ ምልከታ ለማድረግ መታቀዱንም አቶ ሰለሞን ነግረውናል፡፡


አዲሱ እና ከወራት በፊት ከ22 ብር ወደ 100 ብር እንዲያድግ የተደረገው የማተሪዎች የቀን የምግብ ተመንም ቢሆን ዩኒቨርሲቲዎች ከሌሎች ወጪዎቻቸው ወደ ቀለብ ያሸጋሽጉት የነበረውን በጀት በማስተካከሉ ይረዳል በሚል እንጂ፤ አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ለቁርስ፣ ለምሳ እና ለእራት በቂ ነው ማለት አይቻልም ሊሉም ያስረዳሉ፡፡


ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች የምግብ በጀት ስለማይበቃቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የማያስተምሯቸው ተማሪዎች ቁጥር እናስተምራለን በማለት ለትምህርት ሚኒስቴር ይልኩ እንደነበረ መነገሩ ይታወሳል፡፡


አሁን ግን ሁሉም የኒቨርሲቲዎች ያሏቸውን ተማሪዎች ቁጥር እና ሙሉ መረጃ የሚያስመዘገቡበት የመረጃ ቋት(HEMIS) በትምህርት ሚኒስቴር ስለተዘጋጀ የተሳሳተ መረጃ የሚልኩበት እድል የለም ሲሉ ሰለሞን አብረሃ(ዶ/ር) ነግረውናል፡፡


ሙሉ ዘገባውን በድምጽ ያድምጡ..



ማንያዘዋል ጌታሁን ያሰናዳውን በማርታ በቀለ

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page