top of page

መጋቢት 21፣2016  -  የባህር ማዶ ወሬዎች

 

እስራኤል ትናንት ሶሪያ ውስጥ መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት መፈፀሟ ተሰማ፡፡

 

የሶሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ሹሞች እስራኤል በአገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ ክፍል ከባድ ድብደባ መፈፀሟን እንደተናገሩ ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

የሶሪያ ጉዳይ ተከታታዮች በትናንቱ የእስራኤል የአየር ድብደባ ከ40 በላይ የሶሪያ ወታደሮች እና የሔዝቦላህ ታጣቂዎች ተገድለዋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

 

የሶሪያው ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ እስራኤል ሶሪያ ውስጥ እያሰለሰች የአየር እና የሚሳየል ጥቃት እየፈፀመች ነው ይባላል፡፡

 

ከሊባኖሱ የጦር ድርጅት /ሔዝቦላህ/ ጋር ደግሞ በጦር ነገር መፈላለጓ እየተደጋገመ ነው፡፡

 

የሶሪያ መንግስትም ሆነ ሄዝቦላህ የእስራኤል ቀንደኛ ጠላት የሆነችው የኢራን ሁነኛ አጋሮች እና ወዳጆች መሆናቸው ይነገራል፡፡

 

ያደረሰው ጉዳት በዝርዝር ባይጠቀስም ሔዝቦላህም ከደቡባዊ ሊባኖስ ወደ እስራኤል ሰሜናዊ ክፍል ለአፀፋ ሮኬት መተኮሱ ታውቋል፡፡


 

በቅርቡ የዩጋንዳ ጦር ሀይል አዛዥ በመሆን የተሾሙት ጄኔራል ምኡዚ ኬኔሩጋባ ምዝበራ እና የአስተዳደር ብልሹነትን አምርሬ እታገላለሁ አሉ፡፡

 

ጄኔራሉ የፕሬዘዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የበኩር ልጅ ናቸው፡፡

 

ምኡዚ ኬኔሩጋባ ቀደም ሲል የፕሬዘዳንቱ የወታደራዊ ጉዳዮች አማካሪ እንደነበሩ TRT ዎርልድ አስታውሷል፡፡

 

ከዚያ በፊት የዩጋንዳ የምድር ሀይል አዛዥም ነበሩ፡፡

 

ምኡዚ ኬኔሩጋባ በጦር ሀይሉ ውስጥ የሚፈፀምን ምዝበራ እና የአስተዳደር ብልሹነት በጭራሽ አልታገስም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

 

የዩጋንዳ መንግስት ተቃዋሚዎች የጄኔራል ምኡዚን ሹመት የቤተዘመድ ሹመት አድርገው እያዩት ነው፡፡

 

 

በሴኔጋሉ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ የተቃዋሚ ፖለቲከኛ ሆነው የቆዩት የባሲሩ ፌይ አሸናፊነት ተረጋገጠላቸው፡፡

 

ሕገ መንግስታዊው ፍርድ ቤት የባሲሩ ፌይን አሸናፊነት እንዳወጀላቸው አናዶሉ ፅፏል፡፡

 

ባሲሩ ፌይ በምርጫው ያሸነፉት ከተሰጠው ድምፅ ከ54 በመቶ በላይ የሚሆነውን በማግኘታቸው ነው ተብሏል፡፡

 

ዋነኛ ተፎካካሪያቸው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ባ የምርጫ ሽንፈታቸውን የተቀበሉት አስቀድሞ ነው፡፡

 

የአፍሪካ ህብረት ባሲሩ ፌይ የሴኔጋል ፕሬዘዳንት ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደስ ያለዎ መልዕክት ማስተላለፉ ተሰምቷል፡፡

 

ተሰናባቹ ፕሬዘዳንት ማኪ ሳል ቀደም ብሎ ምርጫውን በ9 ወራት ለማራዘም ያደረጉት ሙከራ ፖለቲካዊ ቀውስ እስከመቀስቀስ ደርሶ ነበር፡፡

 

ይሁንና ህገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቱ በጊዜ ማራዘሚያው ህገ-ወጥ ነው ብሎ መወሰኑ አገሪቱን ከብጥብጥ ታድጓታል ተብሏል፡፡

 

 

አሜሪካ በኒጀር የሚገኙ ወታደሮቿን ለማስወጣት ገና ውሳኔ ላይ እንዳልደረሰች የመከላከያ መስሪያ ቤቷ /ፔንታገን/ ቃል አቀባይ ተናገሩ፡፡

 

የኒጀር ወታደራዊ መንግስት አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር የነበራትን የመከላከያ ትብብር ስምምነት አያሻኝም ብሎ ውድቅ ያደረገው በቅርቡ እንደሆነ አናዶሉ አስታውሷል፡፡

 

አሜሪካ በኒጀር ከ1 ሺህ ያላነሱ ወታደሮች አሏት፡፡

 

በምዕራብ አፍሪካዊቱ አገር የድሮን መዘወሪያ ማዕከል እና የአየር ሀይል ሰፈር እንዳላትም ይነገራል፡፡

 

የኒጀር ወታደራዊ መንግስት ቃል አቀባይ የአሜሪካ የኒጀር ቆይታ ግልፅነት የጎደለው ነው ብለዋል፡፡

 

ኒጀር ካለፈው አመት በግልበጣ ስልጣን በጨበጠ ወታደራዊ መንግስት እየተዳደረች ነው፡፡

 

የኒጀር ወታደራዊ መንግስት ስምምነቱ አያሻኝም ቢልም በዚያ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችን ለማስወጣት ገና ውሳኔ ላይ እንዳልተደረሰ የፔንታገን ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ፓት ራይደር ተናግረዋል፡፡

 

 

በአሜሪካ ንብረትነቱ የዩናይትድ አየር መንገድ የሆነ 787 የመንገደኞች አውሮፕላን በአየር ላይ እያለ ከፍተኛ የመንገጫገጭ አደጋ አጋጠመው፡፡

 

አውሮፕላኑ ከእስራኤል ወደ ኒው ጀርሲ በማምራት ላይ ነበረ፡፡

 

6 ሰዎች በመንገጫገጩ አካላዊ ጉዳት ገጥሟቸው ሆስፒታል መግባታቸውን ኒው ዮርክ ፖስት ፅፏል፡፡

 

አውሮፕላኑ በአጣዳፊ ሁኔታ በስቴዋርት አለም አቀፍ ኤርፖርት ለማረፍ መገደዱ ታውቋል፡፡

 

 

የኔነህ ከበደ

 

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

Comments


bottom of page