በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መካከል የማይጨውጦርነት የተደረገው በ1928 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡
ኢጣሊያ በሊቢያና በሱማሊያ ከኢትዮጵያ ክፍል ኤርትራን በቅኝ ግዛትነት ይዛ ከቆየች በኋላ፣ ጠቅላላ ኢትዮጵያን በሃይል ለመውረር ጦርነት ከፈተች፡፡
ከ40 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትነት የመያዝ ፍላጎቷ በአድዋ ጦርነት ቢከሽፍባትም አላማዋን ለማስፈፀም ቀን ጠበቀች፡፡
በምፅዋ ወደብ ፣ በኤርትራ በኩል ወደወሰን ዘመናዊ የጦር ሃይሏን አደራጀች፡፡
የወልወልን ግጭት ሆን ብላ ከቀሰቀሰች በኋላ፣ ተበዳይ ሆና ለመቅረብ ሞከረች፡፡
አከታትላም ዋናው የጦር ሃይሏን ባደራጀችባት ኤርትራ በኩል፣ ወሰን ጥሳ በጥቅምት ወር መቐሌን ያዘች፡፡
ከወራሪው የኢጣሊያ ሃይል ጋር ሲወዳዳር፣ ኋላቀር እና አነስተኛ መሣሪያ ያለው አብዛኛው፣ የኢትዮጵያ ሰራዊት፣ የክተት አዋጁን ተከትሎ፣ ጭብጦ ስንቁን ይዞ፣ ጦርና ጋሻውን አንግቦ ወደዘመቻው ተሰማራ፡፡
ኢጣሊያ፣ በሶማሊያ በኩል ባደራጀችው ዘመናዊ የጦር ሃይል፣ በምሥራቅ በዑጋዴንና በደቡብ በዶሎ በኩል፣ ጦርነት ጀመረች፡፡
ኢትዮጵያም ባላት ሃይል ለመከላከል ሰራዊቷን ወደ ሁለቱም የጦር ግንባር በእግር አጓጓዘች፡፡
ከማይጨው ጦርነት በፊት፣ በርካታ ውጊያዎች ተደርገው ሰራዊትና አዛዞች ሞተዋል፡፡
የጎጃምና የጎንደር ጦር፣ በምዕራብ ትግራይ ተዋግቶ፣ እያሸነፈም፣ እየተሸነፈም በመጨረሻ በአይሮፕላን መርዝ ተጠቅቶ ተበትኗል፡፡
በጦር ሚኒስትሩ የሚመራው ከ50 ሺህ በላይ ይሆናል ተብሎ የተገመተው ጦርና ከወለጋ የተንቀሣቀሰው ጦር፣ በአምባአራዳምና በሌሎች ቦታዎች ተዋግቶ በአውሮፕላን መርዝና በኢጣሊያ ዘመናዊና ከባድ መሣሪያ ጉዳት ስለደረሰበት አዛዦችም ጭምር በጦር ሜዳ ተሰው፡፡

በተምቤን በኩል የዘመተው የሰላሌ፣ የደቡብ ጎንደር፣ የከምባታና የላስታ ጦርም ከታዘዘበት ቦታ ሳይደርስ ኢጣሊያኖች እየቆረጡ አጠቁት፡፡
ኢትዮጵያኖች በጀግንነት ቢዋጉም ጉዳት ስለደረሰባቸው፣ ተተኪ የሌለው ሰራዊት ተዳከመ፡፡
በመጨረሻ ለሰባት ወራት፣ ኢትዮጵዊያኖች ሲፋለሙ ቆይተው፣ ከሞት የተረፉት አዛዦችና ወታደሮች ንጉሠ ነገሥቱ በሚመሩት ጦርነት ለመዋጋት ማይጨው ላይ ተሰበሰቡ፡፡
ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር አብሮ የዘመተው ተዋጊ፣ ከኢጣሊያኖች ጋር ሲወዳደር በቁጥርም፣ በመሣሪያ ጥራትም በብዙ ያንሳል፡፡
ያም ሆኖ የመጨረሻውን ውጊያ ለማድረግ በማይጨው ተሰለፈ፡፡
መጋቢት 22ቀን 1928 በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር በ3 ግንባር ተሰለፈ፡፡
በጄኔራል ባዶሊዩ የሚመራው የኢጣሊያ ሰራዊትም በዘመናዊ መድፎችና ከ70 በላይ በሚደርሱ የጦር አይሮፕላንኖች እየታገዘ ተሰለፈ፡፡
ከንጋቱ 11፡00 ጦርነቱ ተጀመረ፡፡
ውጊያው እንደተጀመረ ኢትዮጵያኖች ኢጣሊያኖች ካምፕ ድረስ ዘልቀው በሚያስደንቅ ጀግንነት ተዋጉ፡፡
ባዶሊዩ ገና በጠዋቱ፣ የጦር አይሮፕላኖቹ በሙሉ ሃይላቸው በቦምብና በመርዝ ጋዝ ኢትየጵያኖቹን እንዲደበድቡ አዘዘ፡፡
ከፍተኛ እልቂት ሆነ፡፡ ምንም መከላከያ የሌላቸው ኢትዮጵያኖች ከውጊያ ውጭ ሆኑ፡፡
የኢትዮጵያ ሠራዊት ምሽት ድረስ ከተዋጋ በኋላ ወደኋላው አፈገፈገ፡፡ ጣሊያኖችም የሚሸሸውን ሠራዊት እየተከታተሉ የመርዝ ጋዝ እየረጩ ፈጁት፡፡
የማይጨው ጦርነት፣ በዚያኑ ዕለት በኢጣሊያኖች ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ፡፡
የማይጨው ሽንፈት፣ ለጠላት አንገብርም ፣ ነፃነታችንን አናስደፍርም ፤ ያሉ ጀግኖች በየጫካውና ሸንተረሩ የአርበኝነት ሥራ እንዲጀመሩ አደረጋቸው፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም ተሰደዱ፡፡
ከአምስት አመት በኋላ፣ ስደተኛው ንጉሠ ነገሥት የእንግሊዝን ዕርዳታ አግኝተው ፤ አርበኞች ጠላታቸውን ተዋግተው፣ ኢጣሊያን ድል መቷት፣ ኢትዮጵያኖች ፣ የሃገራቸውን ነፃነት ከአምስት አመታት በኋላ መለሱ፡፡ የኢጣሊያ ፋሽሽት ወታደሮችና መሪዎች ተገደሉ፡፡ ቀሪዎቹም ታሰሩ፡፡
የተማረኩትና ብዙ ናቸው፡፡
የማይጨው ጦርነት ከተደረገ 89 ዓመት ሆነ፡፡
እሸቴ አሰፋ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
📌Spotify : https://shorturl.at/QG8f2
Comments