መጋቢት 24 2017 - የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መደበኛ ያልሆነን የጎዳና ላይ ንግድ ስርዓት ለማስያዝ ይረዳል ያለውን ደንብ አውጥቷል
- sheger1021fm
- 20 hours ago
- 2 min read
የደንቡን መውጣት ተከትሎም ንግዱ የሚካሄድበት ሰዓት በአምስት ፈረቃ ተከፋፍሎ ይፋ ሆኗል።
በዚሁ መሰረት ከንጋቱ አስራ አንድ ሰዓት እስከ ንጋቱ አንድ ሰዓት የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የአልባሳት እና መጫሚያዎች ንግድ እንደሚካሄድ ተነግሯል።
ከንጋቱ አንድ ሰአት እስከ ረፋዱ ሶስት ሰዓት ደግሞ እንደ ብስኩት ፤ ሻይ ፤ ቡና ፤ የታሸገ ውሃ እና ለስላሳ መጠጦች ያሉ እና ለቁርስ የሚሆኑ ቀላል ያሉ ምግቦች ንግድ ይካሄዳል ተብሏል።
የጫማ ፅዳት ወይም ሊስትሮ አገልግሎትም በዚሁ ሰዓት እንደሚሰጥ የከተማ አስተዳደሩ አመልክቷል።
ከረፋዱ ሶስት ሰዓት እስከ ቀኑ ስድስት የመፅሃፍት ፤ መፅሄቶች እና ጋዜጦች ንግድ እንዲካሄድ ፤ ከቀኑ ስድስት ሰዓት እስከ ስምንት ሰዓት ደግሞ ፤ቀላል ምግቦች በመባል የሚታወቁት እንደ ኬክ ፤ ብስኩት ፤ ሻይ ፤ ቡና ፤ የታሸገ ውሃና ለስላሳ መጠጦች ንግድ እንዲካሄድ ታስቧል።

ከምሽቱ አስራ አንድ ሰዓት እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ተኩል የተጠበሱ ምግቦች ፤ ጁስ ፤ ብስኩት ፤ ኬክ ፤ ሻይ ፤ ቡና ፤ የታሸገ ውሃ እና ለስላሳ መጠጦች ፤ እንዲሁም አልባሳት እና መጫሚያዎች ፤ ቀላል የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ፤ የውበት መጠበቂያ ኮስሞቲኮስች እንዲሸጡ የከተማ አስተዳደሩ መርሃ ግብር አውጥቷል።
ንግዱ የሚካሄድባቸው ቦታዎች ወደፊት እንደሚለዩ የከተማ አስተዳደሩ ተናግሯል።
መደበኛ ያልሆነ የጉዳና ላይ ንግድ ኮንትሮባድን ያበረታታል፤ ለትራፊክ መጨናነቅ እና አደጋም መንስኤ ይሆናል እንዲሁም በህጋዊ ንግዱ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል በሚል ቁጥጥር እንዲደረግበት ሲሞከር የቆየ ነው፡፡
አሁን በከተማ አስተዳደሩ የቀረበው ሃሳብ ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን ምን እንዴት ነው ያያቸው? ስንል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ለሆኑት አቶ ፍስሃ ጥበቡ ጥያቄ አቅርበናል።
አቶ ፍስሃ እንደሚሉት ኢ - መደበኛ በሆነው ንግድ የሚሸጡት ምርቶች በተለይ አልባሳትና ጫማዎች ከአገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተገኙ እንዲሆኑ ነው የታሰበው።
በኮንትሮባንድ የገቡ አልባሳት እና ጫማዎች ወደ ዚህ የንግድ ስርአት እንደማይገቡ ምን ዋስትና አለ? ያልናቸው አቶ ፍስሃ ተከታዩን መልሰዋል።
የኢ - መደበኛ ንግድ ሌላው አሉታዊ ጎን በሚል የሚጠቀሰው በመደበኛ ንግድ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ነው።
ንግድ ፍቃድ አውጥተው፤ ግብር እየከፈሉ የሚሰሩ ነጋዴዎችን ተወዳዳሪነት ይጎዳል በሚል እንደሚነቀፍ ይታወቃል።
ይህንንስ እንዴት አይታችሁት ነው ስንል የቢሮውን ምክትል ህጋዊው ንግድ ፈጽሞ በዚህ አይጎዳም ሲሉ መልሰዋል።
የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች በሚል የተወሰነ አካባቢ ተለይቶ ኢ-መደበኛ ንግዱ እንዲካሄድ ከዚህ ቀደም ሙከራ እንደነበር ይታወሳል።
ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ሰዎች ግን ቅዳሜ እና እሁድ ብቻ በተወሰነ አካባቢ በሚካሄደው በዚህ ንግድ ለመሳተፍ እምብዛም ፍላጎት እንደሌላቸው ሲነገር ቆይቷል።
ምክንያታቸው ደግሞ በዚህ ዓይነቱ ንግድ ብዙም ገበያ የለም ፤ አትራፊም አያደርገንም የሚል ነው፡፡
አሁንስ ወደ ተዘጋጁ ቦታዎች በመግባት በወጣው ፈረቃ ኢ-መደበኛውን ንግድ ለማካሄድ ሰዎች ምን ያህል ፍቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ ስንል የጠየቅናቸው አቶ ፍስሃ መግባት የሚፈልጉ ሰዎችን ብቻ እናስገባለን ብለውናል።
ለመሸጫ የሚለዩ ቦታዎች ይህንኑ ስራ እንዲመራ በተቋቋመው ግብረ ሃይል እየታዩ ለውጥ ሊደረግባቸው ይችላል ተብሏል።
ወደ ፊት እየታየ በኢ-መደበኛ ንግዱ እንዲካተቱ የሚፈቀዱ የስራ ዓይነቶች ሊኖሩ ይችላሉም ተብሏል።
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
📌Spotify : https://shorturl.at/QG8f2
Comentários