መጋቢት 26 2017 - አካባቢን በሚበክል መልኩ አስወግደዋል የተባሉ ተቋማትና ግለሰቦች በድምሩ 80 ሚሊዮን ብር ቅጣት ከፍለዋል
- sheger1021fm
- 11 minutes ago
- 1 min read
በአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ ተግባራዊ በተደረገበት ባለፈው 1 ወር ፍሳሽ እና ቆሻሻን ወንዝና አካባቢን በሚበክል መልኩ አስወግደዋል የተባሉ ተቋማትና ግለሰቦች በድምሩ 80 ሚሊዮን ብር ቅጣት ከፍለዋል፡፡
ከመካከላቸው አንድ ተቋም አንድ ሚሊዮን ብር ቅጣት እንደተጣለበት ሰምተናል፡፡ በተለይ ሳያክሙ ፍሳሽ ቆሻሻዎችን ወደ ወንዞች የሚለቁት ተቋማት ላይ ቅጣቱ ለውጥ እያመጣ ነው ሲል ተቆጣጣሪ መ/ቤቱ ተናግሯል፡፡
ከዚህ ቀደም ፍሳሽ በመልቀቅ ወንዞችንና አካባቢን ሲበክሉ የነበሩ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ መውሰድ ከተጀመረ በኋላ መሻሻሎች እየታየ መሆኑንም የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ተናግሯል፡፡
የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ፍሳሽ በመልቀቅ ወንዞችንና አካባቢን እንዳይበክሉ በሚል የወጣው ደንብ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ሰፊ የግዛቤ ማስጨበጥ ስራ በተለያዩ ጊዜያቶች ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
አሁንም በተለይ እንደ ፋብሪካዎች ፣ ሆስፒታሎች እና ሆቴሎች ያሉ ተቋማት ወንዝን የሚበክሉ ሴፍቲ ታንከር ለመገንባትም ሆነ ሌሎች ማስተካከያዎችን ለማድረግ ወጪ ላለማውጣት በማሰብ እንደሆነ ነግረውናል፡፡
ህጉን ተላልፈው በተገኙት ላይ እርምጃ መውሰድ ከተጀመረ ወዲህ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች መፀዳጃ ቤቶች እና ቆሻሻዎች ወደ ወንዝ በማይቀላቀልበት መልኩ የራሳቸው የፍሳሽ ማስወገጃ ወይም ሴፍቲ ታንከር እየገነቡ መሆኑን አቶ ዲዳ ተናግረዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….. https://www.mixcloud.com/ShegerFM/yjuty/
ፍቅሩ አምባቸው
Comments