መጋቢት 28፣2016 - አሽከርካሪን በመግደል ተሽከርካሪውን ዘርፈው የተሰወሩ 3 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ ፖሊስ ተናገረ
- sheger1021fm
- Apr 6, 2024
- 1 min read
አሽከርካሪን በመግደል ተሽከርካሪውን ዘርፈው የተሰወሩ 3 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ ፖሊስ ተናገረ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ ሶፎኒያስ አስራት የተባለ ወጣት ገድለው ተሽከርካሪውን ዘርፈው የተሰወሩ ማንነታቸው ያልታወቁ ወንጀል ፈፃሚዎችን በ48 ሰዓት ውስጥ ከዘረፉት ተሽከርካሪ ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ወጣቱ ተገግሎ የተገኘው፤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው አሽከርካዎች ማሰልጠኛ አካባቢ ወደ አቦ ቤተ-ክርስቲያን በሚወስደው መንገድ ላይ እንደሆነም ፖሊስ አስረድቷል፡፡
ወጣት ሶፎኒያስ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ/ም ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ናሆም ሆቴል አካባቢ ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ላይ ማንነታቸው የማይታወቁ ሦስት ግለሰቦችን በግል በተደረገ ስምምነት(ያለአፕልኬሽን ምዝገባ) በኮድ 2 ቪትዝ አሳፍሮ ወደ ቦሌ ሚካኤል ለማድርስ መሄዱን ያስረዳው ፖሊስ፤ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ወንጀል ለመፈፀም አቅደው የትራንስፖርት አገልግሎት ፈላጊ መስለው ሹፌሩን በመቅረብ ካሳፈራቸው በኋላ አንገቱን በገመድ አንቀው በመግደል አስክሬኑን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አካባቢ ወደ አቦ ቤተክርስቲያን በሚወስደው መንገድ ላይ በመጣል ተሽከርካሪውን ጨምሮ ሁለት ሞባይል ስልኮችን ዘርፈው መሰወራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ፖሊስ ወንጀሉ ከተፈፀመበት ጊዜ አንስቶ አደረኩት ባለው ብርቱ ክትትል፤ ወንጀል ፈፃሚዎቹ የሰረቁትን ተሽከርካሪ፣ ሦስቱን ዋና ወንጀል ፈፃሚዎች እና የሰረቁትን መኪና እንዲሁም ሶስት አባሪዎቻቸውን ጨምሮ መያዙን ተናግሯል፡፡
በተጨማሪም ከወንጀል ፈፃሚዎቹ እጅ ላይ ባለቤታቸው የማን እንደሆኑ የማይታወቁ 7 የስልክ ሲም ካርዶችን ይዣለሁ ብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ምርመራው መቀጠሉንም ተናግሯል፡፡
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
ShegerFM: @ShegerFMRadio102_1
Comments