መጋቢት 30 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- Apr 8
- 2 min read
በደቡብ ሱዳኑ ተቃዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት ሪያክ ማቻር የሚመራው እና SPLM-IO የተሰኘው የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት ውስጣዊ ክፍፍል እየገጠመው ነው ተባለ፡፡
በዚሁ ክፍፍል የተነሳ 4 የድርጅቱ ከፍተኛ መሪዎች መታገዳቸውን ሱዳንስ ፖስት ፅፏል፡፡
አራቱ የSPLM-IO ከፍተኛ ሹሞች የታገዱት ባልተገባ መንገድ በሴራ ሪያክ ማቻርን ከሀላፊነት ለማባረር ዶልተዋል ተብለው ነው፡፡
ዶክተር ሪያክ ማቻር በወቅታዊው የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በቁም እስር ላይ መሆናቸው ከተነገረ ሰንብቷል፡፡
የታገዱት የSPLM-IO ከፍተኛ ሹሞች ድርጅቱን ለመከፋፈል እያሴሩ ነው ተብሏል፡፡
SPLM-IO ከፖለቲካ ማህበርነቱ በተጨማሪ የጦር ድርጅት ጭምር እንደሆነ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የኒኩሊየር መርሐ ግብሯን እርግፍ አድርጋ እንድትተው በኦማን ቀጥተኛ ንግግር እናደርጋለን አሉ፡፡
ትራምፕ ከኢራን ጋር የኦማኑ ቀጥተኛ ንግግር ይደረጋል ያሉት በዋይት ሐውስ የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
የኢራን ሹሞች ግን ከማዕቀብ እና በጫና ውስጥ ሆነን በጭራሽ ቀጥተኛ ንግግር አናደርግም ሲሉ ቆይተዋል፡፡
ትራምፕ ኢራን በጭራሽ የኒኩሊር ቦምብ ባለቤት እንድትሆን አንፈቅድም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ድርድሩ ፍሬ ካላፈራ ኢራን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ትገባለች የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በኢራን የኒኩሊየር መርሐ ግብር ጉዳይ ትራምፕ የጀመሩትን ዲፕሎማሲዊ ጥረት እንደግፋለሁ ብለዋል፡፡
እስራኤል ራሷ የኒኩሊየር ቦምብ ታጣቂ መሆኗ ይነገራል፡፡
ይሁንና አገሪቱ በይፋ የኒኩሊየር ቦምብ አለኝ ብላ እንደማታውቅ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
በጃፓን አንድ የመጓጓዣ ሔሊኮፕተር ባህር ላይ በመውደቁ የ3 ሰዎች ሕይወት አለፈ ተባለ፡፡
ሒሊኮፕተሩ የበሽተኞች ማጓጓዣ እንደነበር AFP ፅፏል፡፡
ባህር ላይ የወደቀው ሒሊኮፕተር ወደ ፉካኮ ከተማ በማምራት ላይ ነበር ተብሏል፡፡
ሒሊኮፕተሩ አሳፍሯቸው ከነበሩ 6 ሰዎች የ3ቱ ሕይወቱ ማለፏ ተረጋግጧል፡፡
ሌሎቹን ግን በሕይወት ማትረፍ እንደቻለ ተጠቅሷል፡፡
አብራሪውም ሆነ ቴክኒሺያኑ ባለ ልምዶች መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ሔሊኮፕተሩ በምን ምክንያት ሊወድቅ እንደቻለ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም ተብሏል፡፡
የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ ምርመራው እንደተጀመረ መረጃው አስታውሷል፡፡
አልጀርያ መነሻቸውን ከማሊ ያደረጉ አውሮፕላኖች በአየር ክልሏ እንዳይበሩ ከለከለች፡፡
ቀደም ሲል በወሰን አካባቢ የማሊ የቅኝት ሰው አልባ በራሪ አካል (ድሮን) በአልጀሪያ ተመትቶ ከወደቀ በኋላ የሁለቱ አገሮች ውዝግብ እየተካረረ ነው፡፡
አልጀሪያ ድሮኑ ተመትቶ የወደቀው ወደ ግዛቴ ዘልቆ በመግባቱ ነው ብላለች፡፡
ማሊ አልጀሪያ በግዛቴ የሚንቀሳቀሱ ፅንፈኛ እና አማጺ ታጣቂዎችን እየረዳች ነው ነው ሲል በይፋ መክሰሱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የማሊ መንግስት ጦር የቅኝት ድሮን በአልጀሪያ ተመትቶ መውደቁን ተከትሎ ማሊ ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር በአልጀሪያ የነበሯቸውን አምባሳደሮች ወደ አገር ቤት አስጠርተዋል፡፡
ሶስቱ የምዕራብ አፍሪካ መንግስታት የሳሕል መንግስታት ህብረት የተሰኘ ኮንፌዴራላዊ ጥምረት መመስረታቸው ይነገራል፡፡
መንግስታዊ እርምጃዎቻቸው የተናበቡ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
📌Spotify : https://shorturl.at/QG8f2
Comments