በቀይ ባህር የተሰማራው የጣሊያን ባህር ሀይል የየመን ሁቲዎች የሰደዷቸውን ሁለት አጥቂ ሰው አልባ በራሪ አካላት (ድሮኖችን) አወደምኩባቸው አለ፡፡
ጣሊያንም በአሜሪካ መራሹ ጥምረት የባህር ሀይል ባልደረቦቻቸውን እና የጦር መርከቦቻቸውን ወደ ቀይ ባህር ከላኩት አገሮች አንዷ እንደሆነች አናዶሉ ፅፏል፡፡
አሜሪካ መራሹ ጥምረት ሁቲዎቹ በቀይ ባህር ተላላፊ መርከቦች ላይ የሚፈፅሙትን ጥቃት አስቆማለሁ ብሎ ከተሰለፈ ወራት አስቆጥሯል፡፡
የሁቲዎቹን ይዞታም እየደበደበ ነው፡፡
ሁቲዎቹ በበኩላቸው እስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻዋን ካላቆመች የተባባሪዎቿን መርከቦች ማጥቃታችንን አናቆምም በሚለው ውሳኔያቸው እንደፀኑ ነው፡፡
ሁቲዎቹ የኢራን የጦር እና የፖለቲካ ሸሪኮች እንደሆኑ ይነገራል፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር በውጊያው በለስ እየቀናኝ ነው አለ፡፡
ጦሩ የካርቱም ከተማ መንትያ በሆነችው ኦምዱርማን የሚገኘውን የአገሪቱ ዋነኛ የዜና ማሰራጫ ከRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ነጥቄያለሁ ማለቱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የሱዳን መንግስት የኦምዱርማኑን አውታር መልሶ በእጁ ማስገባቱን እጅግ ታላቅ ድል ሲል ጠርቶታል፡፡
ጦርነቱ 11 ወራት ሆኖታል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜም ሰብአዊ ቀውሱን እያከፋው ነው፡፡
በጦርነቱ ከ14 ሺህ የማያንሱ ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ ከ8 ሚሊዮን የሚልቁትን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏቸዋል፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት በሱዳን በረመዳን የፆም ወር የተኩስ አቁም እንዲደረግ በመወሰን ጥሪ ያቀረበው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡
RSF በተኩስ አቁሙ ተስማምቻለሁ ሲል የሱዳን መንግስት ጦር ግን እንዳልተቀበለው ዘገባው አስታውሷል፡፡
የኬንያ መንግስት የፖሊስ መኮንኖቼን ወደ ሔይቲ መላኩን ለጊዜው ትቼዋለሁ አለ፡፡
ቀደም ሲል የኬኒያ መንግስት ሥርዓተ አልበኝነት ወደነገሰበት ሔይቲ 1 ሺህ የፖሊስ መኮንኖችን ለመላክ ተሰናድቻለሁ ብሎ ነበር፡፡
ያም ሆኖ ተቃዋሚዎች ለፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ሒደቱ ተገትቶ ቆይቷል፡፡
ቀደም ሲል ፖሊሶችን ለመላክ እየተዘጋጀሁ ነው ያለው የኬኒያ መንግስት ሹሞች አሁን ለጊዜው ሀሳባችንን ትተነዋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የኬኒያ መንግስት የሀሳብ ለውጥ የተሰማው ወደ አገር ቤት መመለስ አቅቷቸው እንደወጡ ቀሩ ሆኑት የሔይቲው ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪያል ሔነሪ ስልጣን ለቅቄያለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የሔይቲ የፀጥታ መደፍረስ እየባሰበት መምጣቱ ይነገራል፡፡
የባንግላዴሽን ሰንደቅ አላማ የምታውለበልብ መርከብ በሶማሊያ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ ሳትታገት አልቀረችም ተባለ፡፡
የብሪታንያ የንግድ መርከቦች ደህንነት ተከታታይ አካል የባንግላዴሽን ሰንደቅ አላማ የምታውለበልበው መርከብ ባልታወቁ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መግባቷን ደርሼበታለሁ እንዳለ ዘ ኢስት አፍሪካን ፅፏል፡፡
መርከቧ ከሞዛምቢክ ተነስታ ወደ ተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በማምራት ላይ ነበረች ተብሏል፡፡
ከምናልባትም በላይ መርከቧ በባህር ላይ ሽፍቶች ሳትታገት እንዳልቀረች ተገምቷል፡፡
በሶማሊያ የባህር ዳርቻ የባህር ወንበዴዎቹ የመርከብ ጠለፋ የማገርሸት ምልክት እያሳየ ነው፡፡
ከ6 አመታት በፊት የባህር ሽፍቶቹ በቀጠናው ከፍተኛ ችግር ሲፈጥሩ መቆየታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ጆሴፍ ቦሬል እስራኤል የጋዛ ፍልስጤማውያንን ማስራብን እንደ ጦር ስልት እየተከተለች ነው አሉ፡፡
ቦሬል በጋዛ ያንዣበበው የረሃብ አደጋ እስራኤል ሰራሽ ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
እስራኤል ሆን ብላ ለጋዛ ፍልስጤማውያን ሰብአዊ እርዳታ እንዳያልፍ እያከላከለች ነው ሲሉ የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ከስሰዋል፡፡
ለፍልስጤማውያን በጋዛ የባህር ዳርቻ በኩል ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ ጥረት ተጀምሯል፡፡
ይሁንና ቦሬልም ሆነ ሌሎች ይበልጥ ውጤታማው ሰብአዊ እርዳታውን በየብስ ማጓጓዙ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
በጋዛ ከጦርነቱ በተጨማሪ ረሃብም ብዙ ፍልስጤማውያንን ሊያረግፍ ይችላል የሚለው ስጋት አይሏል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments