top of page

መጋቢት 5 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የንግድ ጦርነቱን እያጋጋሉት ነው፡፡


ትራምፕ ከአውሮፓ በሚገቡ የአልኮል መጠጦች ሁለት መቶ በመቶ የሆነ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዩኤስኤ ቱዴይ ፅፏል፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ከአውሮፓ ወደ አሜሪካ በሚመጡ የአልኮል መጠጦች ላይ ሁለት እጥፍ የሆነ የቀረጥ ታሪፍ እጥላለሁ ሲሉ የዛቱት የአውሮፓ ህብረትም ለቀዳሚው የአሜሪካ የቀረጥ ታሪፍ ጭማሪ አፀፋ መመለስ ከጀመረ በኋላ ነው፡፡


አሜሪካ ከውጭ በሚገቡ ብረቶች እና የአልሙኒየም ውጤቶች ላይ የ25 በመቶ የቀረጥ ታሪፍ መጣሏ ለህብረቱ ብቀላ መነሻ ነው፡፡


የህብረቱን እርምጃ ተከትሎ ትራምፕ የቀረጥ ታሪፍ ጭማሪውን አድማስ እንደሚያሰፉት ዝተው ነበር፡፡


የቀረጥ ታሪፍ መበቃቀሉ ወደለየለት የንግድ ጦርነት እያመራ መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡


የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካ ለዩክሬይኑ ጦርነት መግቻ ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ሀሳብ ከቅድመ ሁኔታ ጋር እንቀበለዋለን አሉ፡፡


አሜሪካ ቀደም ሲል ለጦርነቱ መግቻ የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ሀሳብ ማቅረቧን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡


ዩክሬይን የተኩስ አቁሙን መቀበሏን ያረጋገጠችው ቀደም ብሎ ነው፡፡


የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተኩስ አቁሙን እንቀበላለን ቢሉም አብረው ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጣቸው ተሰምቷል፡፡


ፑቲን የተኩስ አቁሙ ወደ አስተማማኝ ሰላም እንዲያመራ በጦርነቱ መነሻ ያነሳናቸውን ችግሮች የሚፈታ መሆኑ ሊረጋገጥልን ይገባል ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡


የዩክሬይኑ ፕሬዘዳነት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ፑቲን በተኩስ አቁሙ ጉዳይ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸውን ተገቢ ያልሆነ ሲሉ ነቅፈውታል፡፡

በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣልባትም ጠይቀዋል፡፡


ፑቲን በኩርስክ ግዛት የሩሲያ ጦር ሙሉ ቁጥጥሩን ማስፈኑን ተናግረዋል፡፡


በዚያ ሙሉ ከበባ ውስጥ የገቡት የዩክሬይን ወታደሮች ምርጫው እጅ መስጠት ወይም ማለቅ ይሆናል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡



የፍልስጤማውያኑ ታጣቂ ቡድን (ሐማስ) የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዛ ፍልስጤማውያንን ለመንቀል ከነበራቸው አቋም ማፈግፈጋቸውን መልካም ሆኖ አግኝቼዋለሁ አለ፡፡


ትራምፕ ቀደም ሲል በጦርነት የወደመችውን ጋዛን መልሶ የቱሪስቶች መናኸሪያ እንድትሆን አድርጎ ለመገንባት ነዋሪዎቿን በአቅራቢያው አገሮች በቋሚነት አስፍሩልኝ ብለው ነበር፡፡


በቅርቡ ግን የአሜሪካው ፕሬዘዳንት መልሰው ፍልስጤማውያንን ማንም ከጋዛ ሰርጥ በሀይል አያፈናቅላቸውም ሲሉ መናገራቸውን አልጀዚራ አስታውሷል፡፡


ይሄም ትራምፕ ከቀደመ አቋማቸው ያፈገፈጉ ያህል መቆጠሩ ተጠቅሷል፡፡


ሐማስ በቃል አቀባዩ አማካይነት ይሄን አቋም ከትራምፕ መስማት መልካም ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል፡፡


የትራምፕ የቀደመ አቋም በተለይም ከመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የበረታ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡


ትራምፕ ከቀደመው አቋማቸው አፈግፍገዋል የተባለበት አስተያየታቸው የተሰማው ልዩ መልዕክተኛቸው ከአረብ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በካታር መነጋገራቸውን ተከትሎ መሆኑ ታውቋል፡፡



በአሜሪካ ዴንቨር በአስገዳጅ ሁኔታ ያረፈ አውሮፕላን በእሳት ተያያዘ ተባለ፡፡


አደጋው የገጠመው የአሜሪካን አየር መንገድ አውሮፕላን መሆኑን ፎክስ ኒውስ ፅፏል፡፡


አውሮፕላኑ በዴንቨር ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በአስገዳጅ ሁኔታ ከማረፉ አስቀድሞ በበረራ ላይ እያለ የሞተር መርገፍገፍ እክል አጋጥሞት ነበር ተብሏል፡፡


ከ170 በላይ ሰዎችን ያሳረፈው አውሮፕላን የሞተር መርገፍገፍ እክል የገጠመው ከኮሎራዶ ስፕሪንግ ወደ ቴክሳስ ዳላስ በማምራት ላይ በነበረበት ወቅት ነው፡፡


በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩ ሰዎች አንዳችም አደጋ ሳይደርስባቸው በአደጋ መውጫው እንዲወርዱ መደረጉ ታውቋል፡፡


ወዲያውኑ አውሮፕላኑ በእሳት መያያዝ ቢጀምርም የአደጋ ተከላካዮች እሳቱን ማጥፋታቸው ተጠቅሷል፡፡


የአሜሪካ ፌዴራል የምርመራ ቢሮ የአደጋውን መንስኤ እያጣራሁት ነው ማለቱ ተሰምቷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page