top of page

መጋቢት 9፣2016 - በቦሌ ኤርፖርት የሚጓጓዙ መንገደኞች፤ ከጉዟቸው ጋር በተያያዘ አጋጠመን የሚሉት ችግር ካለ የሚመለከት ኮሚቴ መቋቋሙ ተሰማ

በአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት በኩል የሚጓጓዙ መንገደኞች፤ ከጉዟቸው ጋር በተያያዘ አጋጠመን የሚሉት ችግር ካለ የሚመለከት እና መፍትሄ የሚሰጥ ኮሚቴ መቋቋሙ ተሰማ፡፡


ኮሚቴው የተዋቀረው በኤርፖርቱ ውስጥ ከሚሰሩት አምስት የመንግስት ተቋማት መሆኑን ሰምተናል፡፡


ተቋማቱም አየር መንገዱ፣ ጉምሩክ፣ የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት፣ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አና የፌደራል ፖሊስ መሆናቸውን ተነግሯል፡፡


በዚህ ጉዳይ የአምስቱም መስሪያ ቤቶች ዋና ሃለፊዎች በየወሩ እንደሚገናኙ ተነግሯል፡፡


የተቋቋመው ኮሚቴ በአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት በኩል የሚጓጓዙ መንገደኞች ከጉዟቸው ጋር በተያያዘ አጋጠመን የሚሉት ችግር ካለ ይመርምራል ተብሏል፡፡


የኢትዮዽያ አየር መንገድ ግሩፕ በአፈፃፀሙ ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል፡፡


የኢትዮዽያ አየር መንገድ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተገናኘ በተለይ ሰሞኑን የቀረበው ቅሬታ በጣም የተጋነነ መሆኑን ተናግሯል፡፡


በአለም አቀፍ ደረጃ መስፈርት መሰረት የሻንጣ መዘግየት፣ መጥፋት፣ መሰበር ከ 1,000 ሻንጣ 5 ቅሬታ የሚጠበቅ ቢሆንም፤ አየር መንገዱ ከ 2.5 በላይ እንዳያልፍ እየሰራ መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው አስረድተዋል፡፡


አሁን ደግሞ ከ 2.2 በታች ለማውረድ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡


ሰሞኑን በአየር መንገዱ ከጉምሩክ ፍተሻ ጋር በተገናኘ እቃ መጥፉቱን በተመለከተ አየር መንገዱ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡


ሰርቀዋል በሚል የተጠረጠሩ ሰራተኞች ወህኒ መውረዳቸውን ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል፡፡


አየር መንገዱ ዳግም እንዲህ ያለ ነገር እንዳይፈጠር በኤርፓርት ስር ካሉ አምስቱ የመንግስት መስሪያቤቶች ጋር በህብረት ለመስራት ቡድን ማቆሙን ተናግሯል፡፡


በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርከት ያሉ አውሮፕላኖች ለመግዛት ማዘዙን ሰምተናል፡፡


70 አውሮፕላኖች ለመግዛት ግዴታ ፈፅሟል፣ 124 አውሮፕላን በትእዛዝ ላይ ነው ተብሏል፡፡



የአለም አቀፍ በረራውን ከፍ ለማድረግ ተርሚናል 2 ላይ መጨናነቅ አለ ለዚህም ማስፉፍያ እየተደረገ ነው ሲሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው አስረድተዋል፡፡


የአውሮፕላን ማቆሚያ ቦታ እጥረት እያጋጠመም ነው ተብሏል፡፡


ቦይንግ 787 አውሮፕላኖች ለ 10 አውሮፕላኖች ብቻ 87 ሚሊየን ዶላር እድሳት ተመድቧል ሲበልም ሰምተናል፡፡


አየር መንገዱ በቢሾፍቱ በ 7.8 ቢሊየን ዶላር ለሚገነባው የአየር ማረፍያ ስንዱ መሆኑን ተናግሯል፡፡


ይህ አየር ማረፊያ ግንባታው ሲጠናቀቅ መቶ ሚሊየን መንገደኛ በዓመት እንደሚያስተናግድ ተነግሮለታል፡፡


ይገነባል የተባለው ኤርፖርት ከቦሌ ኤርፖርት ጋር የሚያገናኘው ፈጣን የባቡር መንገድ ይገነባለታል ተብሏ፡፡



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


bottom of page