ሚያዝያ 14 2017 - በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮና በኦዲተርና የሂሳብ ባለሞያዎች ማህበራት መካከል የተፈጠረው ውዝግብ
- sheger1021fm
- 3 minutes ago
- 2 min read
በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮና በኦዲተርና የሂሳብ ባለሞያዎች ማህበራት መካከል የተፈጠረው ውዝግብ አሁንም አልረገበም፡፡
ውጥረቱን ለማርገብ በማህበራቱ ለቀረበው የእንወያይ ጥያቄ ቢሮው ምላሽ እንደሰጠ ነግሮናል፡፡
የገቢ አሰባሳቢ ቢሮው ለውይይት ለመቀመጥ የማህበራቱን ህጋዊ እውቅና የሚመለከት ማስረጃ እንዲሁም የአባላቱን ዝርዝር በህጋዊ መንገድ አረጋግጣችሁ አምጡ የሚል ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡን አቶ ሰውነት አስረድተዋል፡፡
ቅድመ ሁኔታውን አሟልተው ይመጣሉ ብለን እየጠበቅናቸው ነውም ብለዋል፡፡
ማህበራቱ በበኩላቸው ለቢሮው በደብዳቤ ላቀረብነው የእንወያይ ጥያቄ በደብዳቤ ምላሽ አልሰጠንም፤ይሁንና የተባለውን ቅድመ ሁኔታ እንድናሟላ በስልክ ተነግሮናል፤ በዚህ ጊዜና በዚህ ሰዓት እንወያይ የሚል ቀጠሮ ስላልተሰጠን እሱን እየጠበቅን ነው የሚል ምላሽ የሰጡን ከሶስቱ የኦዲተሮችና የሂሳብ ባለሙያዎች ማህበራት መካከል አንዱ የሆነው የውጭ ኦዲተሮች ማህበር ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሚሊዮን ማሞ ናቸው፡፡

ማህበራቱ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ የገቢዎች ቢሮ እንዲያስተባብል የተጠየቀውን ጉዳይ በተመለከተ ምንም የማስተባብለው ነገር የለም ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የሂሳብ እና የኦዲት ቦርድ ፈቃድ ከተሰጣቸው 863 የሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች መካከል 824ቱ ባለሙያዎች ያቀረቡት የሂሳብ ሪፖርት በማሳነስና በመሰወር የቀረበ በመሆኑ፤ በቦርዱ ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ፍቃድ እስከ መንጠቅ የደረሰ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ቢሮው መጠየቁን ተከትሎ፤ ተፈፀመ የተባለው ስህተት በቦርዱ ሳይረጋገጥ መረጃው በሚዲያ መተላለፉ አግባብነት የሌለውና ሙያውንም ኪሳራ ውስጥ የከተተ ነው ሲሉ የሙያ ማህበራት የሆኑት የኢትዮጵያ የሂሳብ አዋቂዎችና ኦዲተሮች ማህበር፣ የውጭ ኦዲተሮች ማህበርና የአካውንቲንግ ሶሳይቲ ኦፍ ኢትዮጵያ ማህበር ባሳለፍነው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ሰጥተዋል።
ማህበራቱ በመግለጫቸው የገቢዎች ቢሮ ለቦርዱ ባቀረበው ባለሙያዎቹ ይቀጡልኝ የሚለው ጥያቄ ላይ ምንም ቅሬታ እንደሌላቸው ጠቅሰው፤ ይሁንና በሚዲያ የተላለፈበት አግባብ አሳሳች የነበረ በመሆኑ ቢሮው በድጋሚ ማስተባበያ እንዲሰጥበት፤ ጉዳዩን አስመልክቶ የተላለፈው መረጃ ከሚዲያዎችም ሆነ በቢሮው ስር ባሉ የመገናኛ ዘዴዎች የመረጃ ቋት እንዲጠፋልን ሲሉ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
እኛም ለጉዳዩ ማስተባበያ ይስጥ የተባለውን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮን ስለ ጉዳዩ ጠይቀናል፡፡
ምላሻቸውን የሰጡን የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሰውነት አየለ መረጃውን ያሰራጨነው ስራችንን የበለጠ ግልፅ ለማድረግ ነው፤የሰራነው ስህተት ስለሌለ የምናስተባብለው ነገር የለም ብለውናል፡፡
የገቢሮች ቢሮ እርምጃ ይወሰድባቸው ብሎ ለኢትዮጵያ የሂሳብና ኦዲት ቦርድ ጥያቄ ያቀረበባቸው 824 የሂሳብና የኦዲት ባለሙያዎች ጉዳይ አሁንም ድረስ እልባት አላገኘም፤ ጥፋተኛ ናቸው አይደሉም የሚለው በቦርዱ እየተጣራ መሆኑን ሰምተናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….'
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
Comments