ሚያዝያ 14 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- 5 hours ago
- 2 min read
በ88 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ የቀብር ሥነ ሥርዓት በመጪው ቅዳሜ ይፈፀማል ተባለ፡፡
እስከ ቅዳሜም በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የስንብት ሥነ ስርዓት እንደሚከናወን በቤተ ክርስቲያቱ ይፋዊ መግለጫ እንደተጠቀሰ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
አባ ፍራንሲስ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ባጋጠማቸው የአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ እና በከባድ የልብ ድካም መሆኑ ታውቋል፡፡

በሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያኗ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሕልፈት በቫቲካ እና በአለም ዙሪያ ካቶሊካዊያን ዘንድ ከፍተኛ ሐዘን ሆኗል፡፡
የተለያዩ ሀገራት እና መንግስታት መሪዎች እንዲሁም የአለም አቀፍ እና አህጉራዊ ድርጅቶች ተወካዮች በአባ ፍራንሲስ ሕልፈት በእጅጉ አዝነናል እያሉ ነው፡፡
በቀብራቸው ሥነ ሥርዓት ላይም ብዙዎቹ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
በአሜሪካ ለበረራ ተዘጋጅቶ የነበረ የዴልታ አየር መንገድ የመንገደኞች የመጓጓዣ አውሮፕላን የሞተር ቃጠሎ ገጠመው ተባለ፡፡
አደጋው የደረሰው በኦርላንዶ ኤርፖርት እንደሆነ ሬውተርስ ፅፏል፡፡
አውሮፕላኑ ሰራተኞቹን ጨምሮ 300 ሰዎችን አሳፍሮ እንደነበር ታውቋል፡፡
ኤር ባስ ኤ 330 የመንገደኞች አውሮፕላኑ የቀኝ ሞተሩ ቃጠሎ እንደደፈረሰበት ሙሉ ተሳፋሪዎቹ በአደጋ ጊዜ መውጫው እንዲወጡ መደረጉ ተሰምቷል፡፡
በመንገደኞችም ሆነ በአውሮፕላኑ ሰራተኞች ላይ ስለደረሰ ጉዳት የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
የአውሮፕላኑ ሞተር በምን ምክንያት ቃጠሎ እንደገጠመው ለጊዜው አልታወቀም፡፡
የአሜሪካ ፌዴራል የአቪየሽን ባለስልጣን የአውሮፕላኑ የሞተር ቃጠሎ አደጋ በብርቱ ይመረመራል ማለቱ ተሰምቷል፡፡
ከቅርብ ወራት ወዲህ በአሜሪካ የአውሮፕላን አደጋ እየተደጋገመ መምጣቱ ተጠቅሷል፡፡
በጥር ወር በዋሽንግተን አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን ከሔሊኮፕተር ጋር በአየር ላይ በመጋጨቱ 67 ሰዎች መሞታቸውን መረጃው አስታውሷል
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬይን ጋር የሰላም ንግግር ለማድረግ ዝግጁ ነኝ አሉ፡፡
ፑቲን ቀደም ሲል በተናጠል የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ለሳምንት የሚዘልቅ የተኩስ አቁም አውጀው ነበር፡፡
ይሁንና የተኩስ አቁሙ ከ30 ሰዓታት በላይ መዝለቅ አልቻለም ተብሏል፡፡
ለተኩስ አቁሙ መጣስ ሁለቱ አገሮች መወነጃጀል የያዙት ወዲያውኑ እንደሆነ አረብ ኒውስ አስታውሷል፡፡
አሜሪካ የፑቲንን የተኩስ አቁም እርምጃ እሰየው ብላው ነበር፡፡
ቀደም ሲል የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬይኑን ጦርነት በእለት አስቆመዋለሁ ብለው ነበር፡፡
ጦርነቱ ያለ ሁነኛ መፍትኤ ከ3 አመታት በላይ ማስቆጠሩን መረጃው አስታውሷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ፍርድ ቤት ውሳኔ አስፈፃሚ ሀይል ሊኖረው ይገባል ተባለ፡፡
አስተያየቱን የሰነዘሩት የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር እንደሆኑ አናዶሉ ፅፏል፡፡
ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በጋዛ ሰርጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመች ነው ስትል በፍርድ ቤቱ የከሰሰቻት በናሌዲ ፓንዶር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትነት ወቅት ነው፡፡
እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት እያደረሰች ነው በሚል ብትከሰስም ዘመቻዬ የሕልውና ነው የሚል መሟገቻ ታቀርባለች፡፡
የፍርድ ቤቱ ትዕዛዛትም ተከባሪ እንዳልሆኑ ይነገራል፡፡
ናሌዲ ፓንዶር ፍርድ ቤቱ የራሱ ጠንካራ ውሳኔ አስፈፃሚ ሀይል ኖሮት መልሶ ሊደራጅ ይገባል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
Comments