ሚያዝያ 15 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- 12 minutes ago
- 2 min read
የቱርኳ ኢስታምቡል ከተማ በርዕደ መሬት ተመታች፡፡
ኢስታምቡልን ያርገፈገፋት የመሬት ነውጥ በርዕደ መሬት መለኪያ (ሬክተር ስኬል) 6. 2 ሆኖ መመዝገቡን አል አረቢያ ፅፏል፡፡
በአደጋው በሰዎች ላይ ስለደረሰ ጉዳት በዝርዝር የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
በከተማዋ ብዙ ሰዎች ከየህንፃው በመውጣት ውጭ መፍሰሳቸው ተነግሯል፡፡
የርዕደ መሬቱ የነውጥ ማዕከል ከኢስታንቡል ከተማ በስተምዕራብ በ80 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ ስፍራ መሆኑ ታውቋል፡፡
ርዕደ መሬቱ ኢስታምቡልን ከመቱት ከባባድ ርዕደ መሬቶች አንዱ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
የነውጡ ንቅናቄ እስከ ቡልጋሪያዋ ርዕሰ ከተማ ሶፊያ ድረስ ተሰምቷል ተብሏል፡፡

የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መንግስት ተዶልቶብኝ የነበረው የግልበጣ ሴራ መሰረቱ በጎረቤት ኮትዲቭዋር ነበር አለ፡፡
የአገሪቱ የደህንነት ሚኒስትር ማሐማዱ ሳና በተለይም ሁለት የቡርኪናፋሶ የቀድሞ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የሴራው ዋነኞቹ ጎንጓኞች ናቸው ብለው በስም እና በማእረግ እንደጠቀሷቸው ፍራንስ 24 ፅፏል፡፡
የግልበጣ ሴራው አገሪቱን በማተራመስም ዳር እንዲደርስ የተወጠነ እንደነበር ሳና ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በአገሪቱ ሁለት የጦር መኮንኖችን ጨምሮ በርካታ የጦር ባልደረቦች ተይዘው መታሰራቸውን ጉዳዩን ከሚያውቁ ሰምቻለሁ ብሎ የፃፈው ደግሞ AFP ነው፡፡
ቡርኪናፋሶ በአሁኑ ወቅት ራሳቸው ከ3 አመታት በፊት በዳግም ወታደራዊ ግልበጣ ስልጣን ጨብጠው በሚገኙት ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ ትመራለች፡፡
አገሪቱ እንደ ጎረቤቶቿ ኒጀር እና ማሊ እንዳሉ ጎረቤቶቿ የፅንፈኛ ታጣቂዎች ተፅዕኖ የበረታባት ነች፡፡
ቡርኪናፋሶ ፣ ከኒጀር እና ከማሊ ጋር የሳህል አገሮች ጥምረት የተሰኘ ኮንፌዴላዊ ትብብር መመስረቷን መረጃው አስታውሷል፡፡
የዘንድሮው የአለማችን አጠቃላይ ምጣኔ ሐብታዊ እድገት አስቀድሞ ከተገመተው ያንሳል ተባለ፡፡
የአለማችን የዘንድሮው ምጣኔ ሐብታዊ እደገት እንደሚቀንስ በክለሳዬ አረጋግጫለሁ ያለው አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት /IMF/ እንደሆነ ዘ ጋርዲያን ፅፏል፡፡
ድርጅቱ ቀደመ ሲል ዘንድሮ የአለም አጠቃላይ ምጣኔ ሐብታዊ እድገት የ3 ነጥብ 3 በመቶ ይሆናል ብሎ ነበር፡፡
አሁን በክለሳው እድገቱ ከ2 ነጥብ 8 በመቶ እንደማይበልጥ እውቁልኝ ብሏል፡፡
ለአለም አጠቃላይ ምጣኔ ሐብታዊ እድገት ቅናሽ IMF የአሜሪካውን ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕን የታሪፍ ቁለላ እርምጃ በዋና ምክንያትነት ማቅረቡ ተጠቅሷል፡፡
የራሷ የአሜሪካ ምጣኔ ሐብታዊ እድገት ከ2 ነጥብ 7 በመቶ ወደ 1 ነጥብ 8 በመቶ ዝቅ እንደሚል የድርጅቱ ክለሳ አሳይቷል፡፡
የታላላቆቹ አገሮች ምጣኔ ሐብታዊ እድገት በተለያየ ደረጃ ቅናሽ እንደሚያሳይ ተጠቅሷል፡፡
በሕንድ ካሽሚር ግዛት ማንነታቸው በውል ያልተለየ ታጣቂዎች በከፈቱት ድንገት ደራሽ ጥቃት ከ26 የማያንሱ ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ ተባለ፡፡
ጥቃቱ የተፈፀመው በሒማላያ የቱሪቶች መዳረሻ ስፍራ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የጥቃቱ ሰለባዎች በሙሉ የአገር ውስጥ ቱሪስቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡
የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጥቃት አድራሾቹን የገቡበት ገብታችሁ ሕግ ፊት አቅርቡልኝ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ለጥቃቱ በይፋ ሀላፊው እኔ ነኝ ያለ ድርጅት የለም፡፡
የግዛቲቱ የመገንጠል አቀንቃኞች የፈፀሙት ጥቃት እንደሆነ ግምቱ የገዘፈ ነው፡፡
በጥቃቱ ከተገደሉት ሌላ በርካቶች ደግሞ የተለያየ ደረጃ አካላዊ ጉዳት ገጥሟቸው የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡
ሕንድ የካሽሚር የመገንጠል አቀንቃኞች በፓኪስታን ይረዳሉ ትላለች፡፡
ፓኪስታን ደግሞ በሕንድ የሚቀርብባትን ውንጀላ ታስተባብላለች፡፡
የኔነህ ከበደ
Comentários