top of page

ሚያዝያ 21 2017 - ''የጨው ፋብሪካ ያቋቋመው ባለቤት ባልታወቀ ምክንያት ፋብሪካውን ዘግተው ጠፍተውብኛል'' የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ

  • sheger1021fm
  • 9 hours ago
  • 2 min read

ከ4 ዓመት በፊት በ300 ሚሊዮን ብር በአፋር ክልል የጨው ፋብሪካ ያቋቋመው ባለቤት ባልታወቀ ምክንያት ፋብሪካውን ዘግተው ጠፍተውብኛል ሲል የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ተናገረ፡፡


በአፋር ክልል በአፋዴራ ሐይቅ አካባቢ ከ3 ዓመት በፊት ተመርቆ ስራ የጀመረው ቲቲአር አዮዳይዝድ ጨው ማምረቻ ፋብሪካ የተቋቋመው በቱርካና በኢትዮጵያ ባለሀብት መሆኑ በወቅቱ ተነግሮ ነበር፡፡


ፋብሪካው በሰዓት 1,350 ኩንታል በቀን ደግሞ እስከ 20,000 ኩንታል አዮዲን የተቀላቀለበት የገበታ ጨው ያመርታል ተብሎ በምረቃው ወቅት ተነግሮም ነበር፡፡



ፋብሪካውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፣ የወቅቱ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር እና ሚኒስትር ድኤታዎች አፍዴራ ላይ ጥቅምት 15/2013 ተገኝተው እንደመረቁት ይታወሳል፡፡


300 ሚሊዮን ብር ወጥቶበት በቀን 20 ሺህ ኩንታል ጨው ያመርታል ተብሎ የነበረው ቲቲአር የጨው ፋብሪካ ግን ከተዘጋ ከሁለት ዓመት በላይ እንደሆነው የአፋር ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ተናግሯል፡፡


የቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ አይሻ ያሲንን ይህን የተናገሩት ለህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት የማዕድን እና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው፡፡


ቋሚ ኮሚቴው በአፋር ተገኝቶ ቲቲአር እና ኢሲዲየ የጨው ፋብሪካዎችን ተመልክቷል፡፡


ቋሚ ኮሚቴውም ተዘግቶ የተመለከተውን የቲቲአር ጨው ፋብሪካ ምርት ያቆመው በምን ምክንያት ነው የሚል ጥያቄ ለክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቅርቧል፡፡


የቢሮ ሀላፊዋ ወ/ሮ አይሻ ያሲን ፋብሪካው የተዘጋው ባለቤቱ ባልታወቀ ምክንያት ፋብሪካውን ዘግቶ በመጥፋቱ ነው የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡


የቢሮ ሀላፊዋ ለፋብሪካው መዘጋት ባልታወቀ ምክንያት ባለቤቱ ዘግቶ ጠፋ ከማለት ባለፈ ያሉት ነጀር ይኑር አይኑር በፓርላማው መርጃ ላይ አልተጠቀሰም።


ፋብሪካው ስራ በጀመረበት ወቅት ከ1500 በላይ ለአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል መፍጠሩ ተነግሮ ነበር፡፡


የቢሮ ሀላፊዋ ይህንኑ በማስታወስ ፋብሪካው ለአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል ፈጥሮ እንደነበር ጠቅሰው የዚህ ፋብሪካ ችግር ተፈትኖ ማምረት እንዲጀምር የማዕድንና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን እገዛ ጠይቀዋል፡፡


ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ከሚያገባቸው ጋር ሁሉ ውይይት አድርጌ ችግሩ በአስቸኳይ ተፈትኖ ማምረት እንዲችል እሰራለሁ ብሏል፡፡


ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Комментарии


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page