የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ለእስራኤል የብረት ግድግዳ እንሆናታለን አሉ፡፡
የባይደን አስተያየት የተሰነዘረው ኢራን በሶሪያ ደማስቆ የሚገኝ የቆንስላ ፅህፈት ቤቷ ለመመታቱ እስራኤልን እበቀላታለሁ ብላ በተነሳችበት ወቅት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
በደማስቆው ጥቃት ሁለት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጄኔራሎችን ጨምሮ 7 የጦር መኮንኖች ተገድለዋል፡፡
እስራኤል ለደማስቆው ጥቃት በይፋ ሀላፊነት ባትወስድም ኢራን ግን ለዚህ ጥቃት ከእስራኤል ራስ አልወርድም እያለች ነው፡፡
ባይደን ኢራን እስራኤልን ካጠቃቻት ዝም ብለን አናይም ቅጣቷን ታገኛለች ሲሉ መዛታቸው ተሰምቷል፡፡
እንደሚባለው በቀጠናው ለተፈራው የኢራን ጥቃት የእስራኤል እና የአሜሪካ ጦሮች የተጠንቀቅ ደረጃቸውን ከፍ እንዳደረጉ ዘገባው አስታውሷል፡፡
እስራኤል በሐማስ ተይዘው ከሚገኝ ታጋቾች 40ው ሲለቀቁላት በምላሹ 900 ፍልስጤማውያን እስረኞችን በመፍታቱ ጉዳይ እያሰበችበት ነው ተባለ፡፡
አዲሱ የታጋቾች እና የእስረኞች መለዋወጫ የቀረበው በአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት (CIA) ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
እስራኤል ትለቃቸዋለች ከተባሉት እስረኞች 100ዎቹ የእድሜ ይፍታህ ፍርደኞች ናቸው ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በፍልስጤማውያኑ የጦር ድርጅት /ሐማስ/ እጅ ከ130 የማያንሱ እስራኤላውያን ታጋቾች እንደሚገኙ ይገመታል፡፡
በእስራኤል የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ መንግስት በሐማስ እጅ የሚገኝ ታጋቾችን እንዲያስለቅቅ ግፊት እንደበረታበት ይነገራል፡፡
የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ በግንቦቱ ምክር ቤታዊ ምርጫ ይካፈላሉ ተባለ፡፡፡
ቀደም ሲል የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ዙማ በችሎት መድፈር በተፈረደባቸው የ15 ወራት እስር ምክንያት በምርጫው መፎካከር አይችሉም ብሏቸው ነበር፡፡
ይሁንና ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት በዙማ ላይ የተጣለውን ክልከላ አንስቶላቸዋል፡፡
በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረትም ጃኮብ ዙማ በግንቦቱ ምርጫ በተፎካካሪነት ይቀርባሉ፡፡
ከገዢው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC) የፖለቲካ ማህበር ያፈነገጡት ዙማ አዲስ ከተቋቋመው MK የፖለቲካ ማህበር ጋር መወገናቸው ከተሰማ ቆይቷል፡፡
የMK መቋቋም የANC የምርጫ ድምፅ በብዙ እንደሚጋራው ተገምቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን በጋዛ ሰላማዊ ፍልስጤማውያ ላይ የሚደርሰውን እልቂት ለማስቆም በእስራኤል መንግስት ላይ ግፊታቸውን እንዲያበረቱ ተጠየቁ፡፡
ባይደን በእስራኤል መንግስት ላይ ግፊታቸውን እንዲያጠናክሩ የጠየቁት 7 የቀድሞ እና የአሁን የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የባይደን ነቃፊ ሹሞች በዚህ ረገድ ፕሬዘዳንቱ በእስራኤል መንግስት ላይ የሚያደርጉት ግፊት በቂ አይደለም ብለዋል፡፡
የአሁን እና የቀድሞ ሹሞቹ በተለይም ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ያለ አንዳች መሰናክል እንዲገባ ባይደን ግፊታቸውን እንዲያበረቱ ጠይቀዋል፡፡
እስራኤል አዳዲስ የረድኤት አቅርቦት መስመሮችን ከፍቻለሁ ማለቷ ተሰምቷል፡፡
የጋዛ ፍልስጤማውያ በጦርነቱ ቀጥታ ከሚደርስባቸው ጉዳት በተጨማሪ በረሃብም እየተፈተኑ ነው ይባላል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: @ShegerFMRadio102_1
Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments