ሚያዝያ 8፣2016 - በአማራ ክልል በአማካኝ አንድ መፅሐፍ ለ70 ተማሪዎች የደረሰበት አካባቢዎች መኖራቸዉን፤ እንባ ጠባቂ ተቋም አረጋግጫለው አለ
- sheger1021fm
- Apr 16, 2024
- 1 min read
በአማራ ክልል በአማካኝ አንድ መፅሐፍ ለ70 ተማሪዎች የደረሰበት አካባቢዎች መኖራቸዉን፤ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አረጋግጫለው አለ፡፡
የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት፤ ክልሉ የትምህርት ጥራትን በተመለከተ ያደረገውን የክትትል ሪፖርት ለሸገር ራድዮ ተናግሯል፡፡
በዚህም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች የመፅሐፍ ጥምርታ በአማካኝ አንደ መፅሐፍ ለ60 ተማሪ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ አንድ መፅሐፍ ለ70 ተማሪ ነው የሚሰጠው ያሉን የህዝብ እንባ ጠባቂ የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጋሻነው ደሴ ናቸዉ፡፡
ለተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍት በሶፍት ኮፒ ቢሰጥም ተማሪዎች ማንበብያ ማለትም እንደ ስልክ ፣ ታብሌት እና ላፕቶፕ ሰለሌላቸው እየተቸገሩ ነው፤ ይህም በትምህርት ጥራት ላይ ችግር እያስከተለ ነው ተብሏል፡፡
ጽህፈት ቤቱ ሌላው ግኝቴ ነው ያለው፤ በባህርዳር ዙሪያ በ71 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ባረደኩት ክትትልም ከ71ዎቹ ትምህርት ቤቶች 50ዎቹ ምንም ዓይነት መጸዳጃ ቤት የሌላቸው ሲሆን 16ቱ ደግሞ ምንም ውሃ የላቸውም ብሏል፡፡
ይህም ተማሪዎች ለጤና እክል እንዲጋለጡ በር ከፋች ሆኗል ተብሏል፡፡
በባህርዳር ከተማ በተደረገ ክትትልም 57 መምህራን ያልተማሩትን እንደሚያስተምሩ አረጋግጠናል ያሉት ሃለፊው ይህም በፊዚክስ ተመርቀው ጂኦግራፊ እንደ ማስተማር ማለት ነው ብለውናል፡፡
እነዚህ ሁሉ ችግሮች ለትምህርት ጥራት ጉድለት እንቅፋት ሆነዋል መባሉንም ሰምተናል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የዛሬ ዓመት አካባቢ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርቦ የ9 ወር የስራ ክንውን ሪፖርት ሲያቀርብ በኢትዮጵያ ካሉ 47 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አስፈላጊውን ደረጃ ያሟሉት 0.001 መሆናቸው መናገሩ አይዘነጋም፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: @ShegerFMRadio102_1
Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments