ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን የሚገኙ ተፈናቃዮች በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
እነዚህ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቀያቸው ይመለሳሉ ቢባልም እንደታሰበው አልሆነም፡፡
ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡
የፌዴራል መንግስት በበኩሉ የድጋፍ ጥያቄ ከክልሎች ሲቀርብልኝ እሰጣለሁ፤ እያደረኩ ያለሁትም ይህንኑ ነው ብሏል፡፡
ተፈናቃዮቹ ለአራት ወራት ምንም አይነት የምግብም ሆነ ሌሎች ድጋፎች እንዳልተደረገላቸው እና በዚህም የሞቱ ሰዎች እንዳሉ ሰምተናል፡፡
በአንድ የመጠለያ ጣቢያ ብቻ ከ 12 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ተጠልለው እንደሚገኙ እና ከነዚህም ውስጥ አብዛኛው ህፃናት፣ አዛውንት እንዲሁም የሚያጠቡ እናቶች እንደሆኑ ተነግሯል፡፡
መንግስት ‘’የእነዚህ ተፈናቃዮች ሀላፊነት እኔ እወስዳለሁ’’ ቢልም ለተከታታይ አራት ወራቶች ግን ምንም የእህል ዘር አይተው እንደማያውቁ በሶስት የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ነግረውናል፡፡
ችግሩ ከከፋ ረሃብም አልፎ ለሞት እየተዳረጉ እንደሆነ እና ግብረሰናይ ድርጅቶች ቦታው ድረስ በመምጣት ድጋፍ ለማድረግ ቢሞክሩም እንዳልሆነላቸው ሸገር ከተፈናቃዮች ለማወቅ ችሏል፡፡
‘’ሶስት አመት ሙሉ ያለምንም ዘላቂ መፍትሄ እየተሰቃየን ነው መንግስት ሊያየን ይገባል’’ም ይላሉ ተፈናቃዮቹ፡፡
በክልሉ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቀያችሁ ትመለሳላችሁ ተብለው በከፊል ቢመለሱም በድጋሚ ተመልሰው ወደ ደብረብርሃን ቻይና ካምፕ ለመግባት ቢሞክሩም መመለስ እንደማይችሉ እና ስማችሁ መሰረዙን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
አረጋዊያን ህፃናት እንዲሁም ሴቶች ወጥተው መስራት ስለማይችሉ ወጣቶች ወጥተን እንዳንሰራ የመታወቂያ ጉዳይ ሌላ እንቅፋት ሆኖብናል ብለዋል፡፡
ማርታ በቀለ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: @ShegerFMRadio102_1
Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments