top of page

ሚያዝያ  9፣2016 - በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ የሥርጭት ምጣኔ 0.9 ቢሆንም  በቦታ፣ በእድሜ፣ በጾታና በሌሎችም ምክንያቶች ከፍተኛ የስርጭት ልዩነት እየታየ ነው ተባለ

በኢትዮጵያ ያለው አጠቃላይ የኤች አይ ቪ ኤድስ የሥርጭት ምጣኔ 0.9 ቢሆንም  በቦታ፣ በእድሜ፣ በጾታ እንዲሁም በሌሎችም ምክንያቶች ከፍተኛ የስርጭት ልዩነት እየታየ ነው ተባለ፡፡

 

የኤች አይ ቪ መከላከል ስራ ተጋላጭ ዜጎች እና ከፍ ያለ የሥርጭት ምጣኔ የሚታይባቸውን አካባቢዎች በመለየት የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶች አሁንም ሊቀጥሉ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር ተናግሯል።

 

ሀገር አቀፍ የኤች አይ ቪ ኤድስ ፕሮግራም የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም የጋራ ግምገማ  በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

 

ኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ ኤድስ አሁን ያለበትን ስርጭት መጠን ለመቀነስ በመጪዎቹ አራት አመታት የሚተገበር ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅታ በስራ ላይ እንደምትገኝ በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪኤድስ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ያደታ ተናግረዋል።

 

በሀገሪቱ ያለው የኤች አይ ቪ የስርጭት ምጣኔ 0.9 ቢሆንም  በቦታ፣ በእድሜ፣ በጾታ እንዲሁም በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ልዩነቶች እንደሚታይ አቶ ፍቃዱ ጠቅሰዋል፡፡

 

የኤች አይ ቪ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች እና ከፍ ያለ የስርጭት ምጣኔ የሚታይባቸውን አካባቢዎች በመለየት የህክምና አገልግሎቱ በመንግስትና የግል ህክምና ተቋማት በማጠናከር አገልግሎቱን በስፋት በጥራት ማድረስ ያስፈልጋል ብለዋል።

 

ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የማህበረሰብ ችግር ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ዙሪያ አገልግሎቱን ማጠናከር ያስፈልጋል ተብሏል፡፡             

 


ቀደም ሲል በተሰሩ ሥራዎች የተገኘው ስኬት በሁሉም ባለድርሻ አካላት ላይ መዘናጋት እንዲፈጠር በማድረጉ በአሁኑ ወቅት ለሚታየው የበሽታው ስርጭት መጠን መጨመር ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፣ ስርጭቱን ለመቆጣጠር ተቋማት በጋራ መስራት እንዳለባቸው እና በተለይ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉባቸው መጠለያዎች ላይ በማተኮር በጤና ሚኒስቴር የተጀመሩ ስራዎች አሉ ሲሉ አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል፡፡

                       

የUNAIDS ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፍራንሷ በህፃናት ህክምና ላይ ያሉ ክፍተቶችን የማሻሽል፣ በኤች.አይ.ቪ መከላከል አገልግሎቶች ጥምረት ማጠናክር፣ ህጻናት ከኤች.አይ.ቪ ነፃ ህይወታቸውን እንዲጀምሩ ማስቻል እና ሌሎች ፕሮግራሞችን መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

 

ለአራት ቀናት በሚካሄደው ምክክር የሁሉም ክልሎች የኤች.አይ.ቪ ዘርፍ ሀላፊዎችና አጋር ድርጅቶች እንደተገኙ ከጤና ሚኒስቴር ሰምተናል፡፡

 

ምህረት ስዩም

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

Telegram:  @ShegerFMRadio102_1

 

 

 

Comments


bottom of page