ሚያዝያ 9 2017 - በየትኛውም አካባቢ ያለ የኢትዮጵያ ሚሲዮን ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ ግዴታው እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተናገረ፡፡
- sheger1021fm
- 2 days ago
- 1 min read
በየትኛውም አካባቢ ያለ የኢትዮጵያ ሚሲዮን ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ ግዴታው እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተናገረ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ማንኛውም አካባቢ ያለ ሚሲዮን ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አንዱ ቁልፍ ተግባሩ መሆኑን ጠቅሰው ይህን የዘነጋ ካለ ስህተት መሆኑን አምባሳደሩ በመግለጫው ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ዛሬ የኢኮኖሚ ፖለቲካ እና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ላይ ባለፉት 9 ወር የተከናወኑ ስራዎችን ለጋዜጠኞች አብራርተዋል፡፡
ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ወደ 700 ሚጠጉ ኢትዮጵያዊንን ከምያንማር ለመመለስ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመጪዎቹ 10 ቀናት 200 ኢትዮጵያን እንዲመለሱ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ወደ 130 ኢትዮጵያዊያንን ከምያንማር እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉ የተናገሩት ቃል አቀባዩ ባለፉት 9 ወራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 92,000 ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት መመለስ ተችሏል ብለዋል፡፡
በተለያዩ ሀገራት ለመብት ጥሰት የተጋለጡ 13,000 ዜጎች ድጋፍ እንዲያገኙና መብታቸው እንዲከበር ማድረግ መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተናግሯል፡፡
በተለያዩ ሀገራት የሚገኘዩ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች በየሀገራቱ የሚገኙ የሀገሩን ሰዎች ሁኔታ አያውቁም፣ ችግር ሲደርስባቸወም መፍትሄ እንዲሰጥ አያደረጉም ተብሎ ቅሬታ ሲቀርብ ይሰማል፡፡
ይህንኑ ጉዳይ የተጠየቁት አምባሳደሩ የውጪ ሀገር የሚኖሩ ዜጎችን በተመለከተ የትኛውም ሀገር የሚኖር ሚሲዮን ኢትዮጵያዊያን ያሉበትን ሁኔታ መከታተል፤ ድጋፍ ማድረግ እና ተባብሮ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
ከሶማሊያ ጋር ተፈጥሮ የነበረው ውጥረትም መፍታት እንደተቻለ የተናገሩት አምባሳደሩ ይህን የ9 ወር የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ስኬት ነው ብለዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
Comments